ኢትዮጵያ ሕጋዊ እና ታሪካዊ ባህር በር ባለቤትነት የማግኘት ፍላጎት እንዳላት ካሳወቅች ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካካል ውጥረቶች ከተፈጠሩ ሰንብተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ 'የባህር በር የሌላት ሀገር መተንፈስ እንደተሳናት ሀገር ናት' በሚል የገለፁ ሲሆን፤ ይህንንም ጉዳይ ብሐራዊ አጀንዳ እንዲደረግ አድርገውታል፡፡
በዚህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ተፈጥሮ የነበረው መልካም የሚባል ግንኙነት አሁን ላይ ሙለሙሉ ተቀይሮ፤ የጦርነት ድብባብ እንዲይዝ ሆኗል፡፡
ለዚህም ማሳየው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሰሞኑ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ 'በሰሜን ወሎ ወልዲያ ህወሓት እና ኤርትራ ከአማራ ታጣቂዎች ጋር ሆነው ጥቃት ፈፅመውብኛል' ሲል ክስ ማቅረቡ ነው፡፡
'የኤርትራ መንግሥት እና ሕወሓት 'ፅምዶ' ብለው በጠሩት ሕብረት በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለመክፈት በዝግጅት ላይ ናቸው' ሲል፤ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ በፃፈው ደብዳቤ ላይ ከሷል።
በኤርትራ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ያለው ግንኙነት ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በጉልህ እየታየ መምጣቱንም ሚኒስቴሩ በፃፈው ደብዳቤ ላይ ገልጿል፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞትዮስ የተጻፈው ደብዳቤ፤ እነዚህ አካላት እንደ 'ፋኖ' ያሉ የታጠቁ ቡድኖችን በገንዘብ እየደገፉ፣ እያስተባበሩ እና እየመሩ ይገኛሉ ሲልም ይወቅሳል፡፡
ይህም በተለይም በህወሓት እና በኤርትራ መንግሥት የተፈጠረው 'ፅምዶ' የተሰኘው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በሚል የጦር ዝግጅት እየተደረገብኝ ይገኛል ሲልም ነው መንግሥት አቤቱታውን ያሰማው፡፡
ይህንን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መግለጫ ተከትሎ የኤርትራ መንግሥት ለክሱ ምላሽ የሰጠ ሲሆን፤ "የጦርነት ፀብ አጫሪነት ነው" ሲል ገልፃልታል፡፡
ህወሓትም በተመሳሳይ ክሱን ውድቅ አድርጎ ምላሽ ያለውን ለተባበሩት መንግሥታት የላከ ሲሆን፤ በተለይም የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አለመተግበሩን አፅዕኖት ሰጥቶበታል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት 'የፕሪቶሪያን ስምምነት ከመተግበር ይልቅ በፈጠራ ታሪኮች ህወሓት ላይ የሥም ማጥፋት ዘመቻ በማካሄድ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት ለማሳት እየሞከረ ነው' በማለት፤ ህወሓት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሓፊ በላከው ደብዳቤ አመልክቷል።
በተጨማሪም የፕሪቶርያ ስምምነት እየተጣሰ ነው ብሎ የተለያዩ ነጥቦች ያነሳው ህወሓት፤ ተፈፃሚነቱ ለማረጋገጥ አዲስ ዓለም አቀፋዊ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ አሳውቋል፡፡
ሀሳባቸዉን ለአሐዱ የሰጡት ፖለቲካኛው አበበ አካሉ አሁን ላይ በህወሓት እና በኤርትራ መንግሥት መካካል ጥምረት ተፈጥሯል በሚል የሚቀርበዉ ክሰ ቀድሞ በፌደራል መንግሥት ከተሰራው ስህተት ጋር አንድ ዓይነት ነው ይላሉ፡፡
"ይህንኑ ስህተት የፌደራል መንግሥትም ሰርቶት ነበር" ያሉት አቶ አበበ፤ "በፖለቲካ ቋሚ ወዳጅም ሆነ ቋሚ ጠላት የለም" ብለዋል፡፡
አቶ አበበ አክለዉም፤ ቀድሞውን ህወሓት ትጥቅ ይፍታ ሲባል በአግባቡ ባለመፈፀሙና ስምምነቱ ችግር ውስጥ በመውደቁ የመጣ ችግር መኖሩ መታወቅ አለበት ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
ባሳለፍነው ሰኞ ዕለት በተከፈተው ምክር ቤት ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ፤ "ኢትዮጵያ ዕጣ ፋንታዋ እና መፃኢ ዕድሏ ከዓባይ እና ከቀይ ባሕር ጋር በእጅጉ የተገናኘ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ፍትሕን ባልተከተለ መንገድ እና ሕዝብን ባላማከለ ባላሳተፈ አግባብ ተገልላ ቆይታለችም ብለዋል።
"መንግሥት ይህንን ለማስተካከል በመሥራት ላይ ይገኛል" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ የባሕር በር ጉዳይ የዓለም አቀፍ የመነጋገሪያ ሀሳብ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በሰኞ ዕለቱ ፓርላማ ውሎ ላይ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ "የቀጣናችንን የጋራ የመልማት ፍላጎት ያገናዘበ ትብብር እና ትስስርን ለማጠናከር ዲፕሎማሲያዊ እና ሰላማዊ ጥረቶች ይደረጋሉ" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
"የአካባቢያችንን ሰላም ለማረጋገጥ አለመግባባቶችን በዲፕሎማሲያ መንገድ ለመፍታት መንግሥት አበክሮ ይሰራል" ብለውም ነበር፡፡
ይህንን የፕሬዝዳንቱን ንግግር ተከትሎ የኤርትራ መንግሥት የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገፃቸው በሰጡት ምላሽ፤ የፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴን ንግግር "ግራ የሚያጋባ እና ለማሰብ የሚከብድ" ሲሉ ገልጸውታል፡፡
ጉዳዩ በብዙ ነውጦች እና ችግሮች በሚታመሰው የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ላይ አላስፈላጊ እና ሊወገድ የሚችል ግጭት የሚቀስቀስ ይዘት እንደሚኖረውም ጠቅሰዋል።
ይህ ዓይነቱ ምልልሶች እየፈጠሩት ያሉት ውጥረት ወደ ጦርነት እንዳያመራ የብዙዎች ስጋት ሲሆን፤ ጉዳዩ በጥሩ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ የሚጠይቁ በርካቶች ናቸው፡፡
በተጨማሪም በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ እየተወዛገቡ ያሉት መንግሥት እና ህወሓት፤ ወደሌላ ዙር ጦርነት ተመልሰው እንዳይገቡ በበርካቶች ዘንድ ስጋት ፈጥሮ ይገኛል፡፡
የአንድ ኢትዮጵያ አንድነት ፖርቲ ፕሬዝዳንት ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር፤ "አሁን ባለው ዉስጣዊ ችግር ጦርነት መክፈት አክሳሪ ሊሆን ይችላል" ይላሉ፡፡
በተለይም ከሰሞኑ ውጥረቱ እየተባባሰ መቀጠሉ ነገሩን ወደ ከፋ ደረጃ እንዳያደርሰው ስጋታቸውን የገለፁት ፖለቲካኛው፤ ኢኮኖሚው ላይም የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ዘሪሁን "የባህር በር ጥያቄ እንደ ፖለቲካ አቋማቸው ይዘውት ያሉት መሆኑን ይናገራሉ፤ ነገር ግን የባህር በር ጉዳይ የፖለቲካ ትፍር ማግኛ መሆን የለበትም" ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ሀሳቡን የሚደገፍ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፤ ነገር ግን በፀና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማምጣት መሠራት አለበት እንጂ በጉልበት የሚሆን አይደለም ሲሉም አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተባበሩት መንግሥታት ከሰሞኑ በላከው ደብዳቤም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ገንቢ ግንኙነት እና ትብብር እንዲኖር ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት እንዲቀጥል ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡
የባህር በር ጉዳይ መንግሥት በዋና አጀንዳነት እንደያዘው በፓርላማ መክፍቻ ወቅትም በግልፅ የተቀመጠ ጉዳይ መሆኑን መመልከት ይቻላል፡፡
ይሁን እንጂ ይህንን ለማሳካት የተደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ግልፅ መደረግ እንዳለባቸው የሚያነሱም በርካቶች ናቸው፡፡
የባህር በር የማግኘት ጉዳይ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ብቻ መፈታት አለበት ተባለ
