መስከረም 30/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) መንግሥት በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ ማናቸውም አይነት የደረቅ እና የፈሳሽ ጭነት እና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፤ ከጉምሩክ ቀረጥ ነጻ ወደ ሀገር እንዲገቡ መፍቀዱን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ያላት መሆኑ ቢታወቅም፤ ለዘመናት የዚህ የተፈጥሮ ሃብት ተጠቃሚ ሳትሆን መቆየቷን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

ይህንን ሁኔታ ለመለወጥ መንግሥት ሲያደርግ የቆየው እልህ አስጨራሽ ጥረት ተሳክቶ በቅርቡ በካሉብ አካባቢ የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል ኢንዱስትሪ ተመርቆ የተፈጥሮ ጋዝ የማምረት ሥራ በይፋ መጀመሩን አስታውሷል።

በመሆኑም ይህን ምርት ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ቤንዚንና ናፍታ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን የተፈጥሮ ጋዝ በሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች መተካት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስታውቋል።

የተፈጥሮ ጋዝ የሚያመነጨው በካይ አየር እጅግ በጣም ዝቅተኛ የሆነ፤ ለተለያየ የኃይል ምንጭ አገልግሎት ሊውል የሚችል፤ በኃይል አጠቃቀም ረገድ ውጤታማነት ያለው መሆኑን ነው የገለጸው፡፡

የተፈጥሮ ጋዝ በኢትዮጵያ የሚመረት በመሆኑ ለነዳጅ ግዥ ታወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀር በመሆኑ መንግሥት የተፈጥሮ ጋዝ አጠቃቀምን ለማበረታታት መወሰኑን ሚኒስቴሩ ለአሐዱ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በዚህም መሰረት ይህ መመሪያ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ሙሉ በሙሉ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ ማናቸውም አይነት የደረቅ እና የፈሳሽ ጭነት እና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከጉምሩክ ቀረጥ ነጻ ወደ ሀገር እንዲገቡ መፈቀዱን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ስለዚህ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በተወሰነው መሠረት ይህ መመሪያ ከወጣበት ቀን በፊት በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እና በሌሎች ተቋማት ወደ ሀገር እንዲገቡ ከተፈቀደላቸውና በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገር ከሚገቡት በስተቀር በቤንዚን እና በናፍጣ የሚሰሩ የጭነት እና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር እንዳይገቡ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ ሚኒስቴሩ አሳስቧል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ