ጥቅምት 24/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች እና አለመግባባቶች እንዲፈቱ፣ ሞት እና መፈናቀል እንዲቆም እንዲሁም፤ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከመወቃቀስ ይልቅ ኃላፊነትን መወጣት እንዲቀድም የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳስቧል።

"መወቃቀስ እውነተኛ ዘላቂ ሰላም አያመጣም" ሲሉ ለአሐዱ የተናገሩት የጉባኤው የሕዝብ ግንኙነት እና የሚድያ ክፍል ኃላፊ መጋቢ ይታገሱ ኃይለሚካዔል፤ ሁሉም ማኅበረሰብ ክፍል የራሱን፣ የቤተሰቡን፣ የአካባቢውን ብሎም የሀገሩን ሰላም የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል።

ስለሆነም "ሁላችንም ሰላምን የመጠበቅ፣ ሰላምን የማስፈን እና ሰላምን የማጽናት ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል" ብለዋል።

በማስከተልም፤ "ሰላም ከሌሎች የምንጠብቀው ሳይሆን ራሳችን የምናመጣው ነው፤ እያንዳንዱ ማኅበረሰብ በየአካባቢው የሰላም ዘብ መሆን አለበት" ያሉ ሲሆን፤ ሰላም የአንድ ጊዜ ተግባር ሳይሆን በየቀኑ ልንንከባከበው የሚገባ የሕይወታችን ክፍል ነው ሲሉ ገልጸዋል።

መንግሥት 'ሰላም በማደፍረስ ጥቅም እናገኛለን' በሚል የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ አካላትን በሕግ መቆጣጠር እንዳለበትም መጋቢ ይታገሱ አሳስበዋል።

በተጨማሪም፤ ሰላማዊ ግንኙነቶችን ለማጠናከር የሚያስችሉ የሰላም ኮንፈረንሶችን በማዘጋጀት ለሕዝቡ ግንዛቤ የመስጠት ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሁለት ወራት አንድ ጊዜ ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ በማካሔድ፤ ለሰላም መስፈን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ኃላፊው አብራርተዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ