ጥቅምት 22/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የክብር ዶክተር አርቲስት ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) በኢትዮጵያ ቀዳሚ ለሆነው ለአብነት የማህበረሰብ ትምህርት ቤቶች፤ የግጥምና የዜማ ሥራዎቻቸውን በዛሬው ዕለት በይፋ አስረክበዋል፡፡

አርቲስቱ በሥማቸው በተሰየመው የኪነ-ጥበብ ማዕከል ውስጥ የአብነት የማህበረሰብ ትምህርት ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ነው ሥራዎችቸውን ያስረከቡት፡፡

የልዩ ፍላጎት ትምህርት መርሃ ግብርን ጨምሮ በሁሉም ዕድሜ ክልል የሚገኙ ተማሪዎች፤ ያላቸውን ምቹና ተስማሚ እምቅ አቅምና በዋጋ ሊተመን የማይችል አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በማሰብ ለተቋቋመው አብነት የማህበረሰብ ት/ቤቶች አርቲስቱ ሥራቸውን ማስረከባቸው ተገልጿል።

Post image

በኪነ ጥበብ ማዕከሉ በተካሄደው ፕሮግራም ላይ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ወርቅነህ፤ የአብነት አካዳሚ ለአርቲስት ተስፋዬ አበበ እስከ ሕይወት ዘመናቸው ድረስ በተለያየ መንገድ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።

ስለ አርቲስቱ ሥራ እና ለትምህርት ቤታቸው ስለተበረከተው ሥራም ምስጋና አቅርበዋል።

በመድረኩ በማዕከሉ ተማሪዎች የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ለታዳሚዎች ቀርበዋል።

በመርሀ ግብሩ የአብነት ማሕበረሰብ ትምህርት ቤቶች ቦርድ አባል አርቲስት አብራራ አብዱ፣ ተጋባዥ እንግዳ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ኤፍሬም ለማ (ዶ/ር) እንዲሁም ጋዜጠኛ ሱራፌል ዘላለም ተገኝተዋል።

በግል ይተዳደር የነበረው 'አብነት አካዳሚ' "ትምህርት ቤቶች የህብረተሰቡ ሀብት ናቸው" በሚል አስተሳሰብ የተቋሙን የባለቤትነት ድርሻ ሙሉ በመሉ የሕብረተሰቡ እንዲሆን በማሰብና፤ ለአካባቢው ማሕበረሰብ የሚሰጠውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሰኔ 28 ቀን 2017 "አብነት የማህበረሰብ ትምህርት ቤቶች" በሚል ስያሜ ዳግም በይፋ መመስረቱን አሐዱ ከዚህ በፊት መዘገቡ የሚታወስ ነው።

አብነት አካዳሚ ላለፉት 12 ዓመታት ከጥንስሱ ዓላማውና ተልዕኮው ወጥኖ ሲነሳ፤ ትምህርትን ለሁሉም የአካባቢው ሕብረተሰብ ሕጻናት በጥራትና በፍትሃዊነት ተደራሽ በማድረግ፤ የሀገር ተረካቢ ትውልድ በእውቀት፣ በክህሎትና በመልካም ሥነ-ምግባር የማነጽ ተልዕኮ አንግቦ እንደነበረ ተገልጿል።

የክብር ዶክተር ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ለ34 ቲያትሮች የተውኔት ፅሁፍ እንዲሁም 500 ዘፋኞች ግጥም ያበረከቱ አንጋፋ የኪነ-ጥበብ ባለሙያ ሲሆኑ፤ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ለዚህ አበርክቷቸው የሕይወት ዘመን ሽልማት እና የክብር ዶክትሬት ሽልማት እንደሰጣቸው ይታወሳል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ