ጥቅምት 24/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ማለትም ከሐምሌ 1 ቀን 2017 እስከ መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የወንጀል ድርጊቶችን ለመፈጸም የተንቀሳቀሱ 229 ተጠርጣሪዎችን ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት "እጅ ከፍንጅ" በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
ፖሊስ ይህን ስኬት ያስመዘገበው በሕብረተሰቡ ጥቆማ አማካይነት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በከተማዋ የሚስተዋለው የወንጀል ድርጊት 42 በመቶ መቀነሱ ተነግሯል።
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ፤ በተጠቀሰው የሦስት ወር ጊዜ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ወንጀለኞች በተጨማሪ በድንገተኛ ፍተሻዎች እንዲሁም በማኅብረተሰቡ ጥቆማ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው እንደ ሺሻ ያሉ አነቃቂ እና አደንዛዥ ዕፆች እና እጾቹን ለመጠቀም የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች በኤግዚቢትነት ተይዘዋል ብለዋል።
በተጨማሪም ፖሊስ 1 ሺሕ የሚደርሱ የቁማር እና ሺሻ ማጨሻ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ ማዘጋታቸውን ኮማንደር ማርቆስ ገልጸዋል።
ኮማንደር ማርቆስ በሕብረሰብና በፖሊስ መካከል ያለው የተቀናጀ ሥራ የአዲስ አበባ ከተማን ሰላም እና ፀጥታ "ጥሩ በሚባል ደረጃ" አድርሰውታል ያሉ ሲሆን፤ ይህንን የጋራ ሥራ ለማጠናከርም ፖሊስ መድረክ ዘርግቶ በርካታ ውይይቶች አካሂዷል ብለዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በመዲናዋ በሦስት ወራት ውስጥ ብቻ 229 ወንጀል ፈጻሚዎች "እጅ ከፍንጅ" መያዛቸው ተገለጸ