ጥቅምት 17/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ዘላቂና የተረጋጋ ሰላም እንዲኖር፣ መንግሥት የሕግ የበላይነትን በማስከበርና የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በማረጋገጥ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ አሐዱ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች አሳስበዋል።

ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም የግጭት መንስኤዎች ላይ ያተኮረና ሁሉን አሳታፊ የሆነ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጠበቃና የሕግ ባለሙያ አቶ ቶማስ አየለ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ ሰላም መደፍረሱ "የታፈነ ድምፅ" ውጤት ነው። በመሆኑም፣ መንግሥት የዜጎችን መብት ባከበረ መንገድ የሕዝብ ጥያቄዎች የሚመለሱበትን ሥርዓት በመዘርጋት የጋራ መግባባት እንዲፈጠር መሥራት አለበት።

አቶ ቶማስ ችግሮች እንዳይከሰቱ ለመከላከል የችግሮችን መንስኤዎች ለይቶ ማወቅና ሁሉን ያሳተፈ የኢኮኖሚ ሥርዓት ማንበር፣ እንዲሁም መደማመጥ የሚቻልበት ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ አብራርተዋል።

በተለይም የሕግ ማስከበር ሥራው የዜጎችን ሰብዓዊ መብት መከበር በሚያጎላ መንገድ መከናወን እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተውበታል።

ሌላኛው ጠበቃና የሕግ ባለሙያ አቶ ባንተወሰን ግርማ፤ በየአካባቢው ባሉ ግጭቶች ምክንያት ዜጎች ለተለያዩ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና መሰል ችግሮች እየተጋለጡ እንደሆነ ተናግረዋል።

“ሰላም እንዲረጋገጥ የሕብረተሰቡን ፍላጎት ያማከለ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል” ያሉት የሕግ ባለሙያው፤ የሃይማኖት አባቶች፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የማቀራረብ ሥራ መሠራት አለበት ብለዋል።

"እንዲሁም በየዘርፉ የሚገኙ ባለሚናዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ሲችሉ እና መንግሥት የሕግ የበላይነትን ሲያረጋግጥ ሰላምን ማስፈን ይቻላል" ሲሉ አብራርተዋል።

አሐዱ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች መንግሥት በኢትዮጵያ በአንዳንድ ቦታዎችና ክልሎች ላይ የሚስተዋሉ ግጭቶች ለዘላቂ ሰላም እንዳያሰጉ የበላይነቱን በመያዝ፣ የችግሮችን መንስኤ በመለየት፣ መመሪያዎችን እና ሕጎችን ባከበረ መልኩ ወደ ውይይት ማምጣት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተውበታል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ