ጥቅምት 17/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ በባንክ የሚካሄድ አጠቃላይ የገንዘብ ዝውውር ቅናሽ ማሳየቱን የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ማኅበር "ባካሄድኩት ጥናት አረጋግጫለሁ" ብሏል።
በማኅበሩ ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ተመራማሪ ናስር የኑስ (ዶ/ር) ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ በተለይ ከ2012 ዓ.ም. መጨረሻ ወራት አንስቶ፣ በይበልጥ ደግሞ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ የገንዘብ ዝውውር (ትራንዛክሽን ባንኪንግ) አገልግሎት የሚጠቀሙ ደንበኞች ቁጥር እየቀነሰ ነው።

ለዚህ የገንዘብ ዝውውር መቀነስ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች የጠቀሱት ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ተመራማሪው፤ የዜጎች የገቢ ማሽቆልቆል፣ አልፎ አልፎ የሚታዩ ግጭቶችና ጦርነቶች እልባት አለማግኘት፣ የሥራ አጥ ቁጥር መጨመር፣ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ችግር እንደሆኑ ዘርዝረዋል።
ተመራማሪው ይህንን እያሽቆለቆለ ያለውን የገንዘብ ዝውውር ለማነቃቃት ባንኮች ሊተገብሯቸው ይገባል ካሏቸው የመፍትሔ እርምጃዎች መካከል፤ ባንኮች ለገንዘብ ዝውውር የሚቆርጡትን የአገልግሎት ክፍያ መቀነስ፣ የዜጎችን የዲጂታል የገንዘብ ዝውውር ግንዛቤ ማሳደግ፣ ባንኮች አስተማማኝ፣ ግልጽና አማራጭ የሆኑ የዲጂታል የመገበያያ መተግበሪያዎችን በሚፈለገው ልክ ማቅረብ እና ባንኮች ለደንበኞች ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚሉት ይገኙበታል።
ዶክተር ናስር አክለውም፤ መንግሥት በኢትዮጵያ በየጊዜው የሚፈጠሩ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮችን ለመቀነስ ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ