#አሐዱ_ዓለም_አቀፍ_መረጃዎች

ጥቅምት 17/2018 (አሐዱ ሬዲዮ)

በካሜሮን በተካሄዱ ተቃውሞዎች አራት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

እሁድ ዕለት በካሜሮን የንግድ ዋና ከተማ ዱዋላ በተካሄደው ተቃውሞ ቢያንስ አራት ሰዎች በጥይት ተገድለዋል፡፡

በጥቅምት 12 የተካሄደው ምርጫ ውጤት በተመለከተ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ መንገዶችን ዘግተዋል።

በተጨማሪም ተቃዋሚዎቹ በከተማው በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም በርካታ የጸጥታ ሃይል አባላት መቁሰላቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ፖሊስ ተቃዋሚዎችን ለመበተን በአስለቃሽ ጭስ እና በሌሎች አማራጮች ምላሽ መስጠቱን አልጀዚራ ዘግቧል።

ተቃውሞዎቹ የተነሱት በጥቅምት 12 የተካሄደው ምርጫ ከፊል ውጤቶች ይፋ ከተደረጉ በኋላ ነው።

ከፊል ውጤቱ የ92 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ቢያ ለስምንተኛ ጊዜ የስልጣን ዘመን ሊያሸንፍ እንደሚችል ጠቁሟል።

የናይጄሪያ መንግሥት 16 የጦር መኮንኖችን ለመፈንቅለ መንግሥት በማሴር ጠርጥሮ ማሰሩን አስታወቀ

የናይጄሪያ መንግሥት ዋና የጦር አዛዡን ጨምሮ 16 የጦር መኮንኖችን ለመፈንቅለ መንግሥት በማሴር ጠርጥሮ ማሰሩን አስታውቋል፡፡

የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኒፉ አስራ ስድስቱ የጦር መኮንኖች በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው እንዲመረመር አዘው፤ በምትካቸው ሌሎች የጦር መኮንኖች ሾመዋል፡፡

በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው የተደናገጠው የናይጄሪያ መንግሥት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ኦክቶበር 1 ሊከበር የታሰበውን የነጻነት ቀን ክብረ-በዓል መሰረዙ ታውቋል፡፡

አዳዲሶቹ ሹመኞች ኃላፊነታቸውን በብቃት ይወጣሉ ብለው እንደሚያምኑ የገለጹት ፕሬዝዳንት ቦላ፤ "መንግሥት የናይጄሪያን ብሄራዊ የጸጥታ መዋቅር ለማጠናከር የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል" ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

የአይቮሪ ኮስት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የ83 ዓመቱ ዋታራ በከፊል ውጤቶች እየመሩ መሆኑ ተገለጸ

በምዕራብ አፍሪካዋ ሀገር አይቮሪ ኮስት በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ፣ የአሁኑ ፕሬዝዳንት አላሳን ዋታራ በከፊል ይፋ በተደረጉ ውጤቶች ከፍተኛ መሪነታቸውን ይዘዋል።

ዋታራ በሕገ-መንግሥቱ ለውጥ አማካኝነት ለ4ኛው የስልጣን ዘመን ለመወዳደር ማሰባቸው ውጥረትንና ተቃውሞን በፈጠረበት ሁኔታ፣ ድል ሊቀዳጁ እንደሚችሉ ይጠበቃል።

ይህ ከፊል ውጤት የተገለጸው ተቃዋሚዎች ምርጫውን ‘ያልተሟላና ሕገወጥ’ ሲሉ በሰፊው ተቃውሞ በጠሩበት ወቅት ነው፡፡

ዋና ተቃዋሚ እጩዎች ቀደም ብለው ከእጩነት ዝርዝር ራሳቸውን ማግለላቸው ውጥረቱን ካባባሱት ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡

አንዳንድ ተፎካካሪዎች ውጤቱን እየተቀበሉ ቢሆንም፣ ተንታኞች ግን በፖለቲካዊ ውዝግቦች የተሞላው ይህ ምርጫ ሀገሪቱን ወደ ቀድሞው የድህረ-ምርጫ ቀውስ ሊመልስ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

ፕሬዝዳንት ዋታራ በበኩላቸው፣ የሀገሪቱን መረጋጋት እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስቀጠል ቅድሚያ እንደሚሰጡ ገልጸዋል ሲል የዘገበው አልጀዚራ ነው።

የብራዚል ፕሬዝዳንት ከአሜሪካ ጋር የንግድ ስምምነት ዋስትና እንዳገኙ ገለጹ

የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ከአሜሪካ አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ የንግድ ስምምነት ላይ መድረስ የሚያስችል ዋስትና እንዳገኙ ተናግረዋል።

ሉላ በማሌዥያ በተካሄደው የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ህብረት ጉባኤ ጎን ለጎን መግለጫ ሰጠዋል። በመግለጫቸው ከትራምፕ ጋር ያደረጉት ውይይት በጥሩ ሁኔታ መከናወኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ከሚታሰበው ፍጥነት በላይ ስምምነት እንደሚደረስ ተናግረዋል። አሜሪካ በብራዚል ምርቶች ላይ 50 በመቶ ታሪፍ ጥላለች።

ፕሬዝዳንቱ በቅርቡ አሜሪካ በብራዚል ላይ የወሰደቻቸው ውሳኔዎች የተሳሳቱ መሆናቸውን መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ነገር ግን ከትራምፕ ጋር በማንኛውንም ጉዳይ ለመወያየት ፈቃደኛ እንደሆኑ ጠቁመዋል።

አሜሪካ እና እስራኤል በጋዛ የመሸገውን ሃማስ ሙሉ ለሙሉ ለማውደም መስማማታቸውን የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ተናገሩ

ሚኒስትሩ፤ ሃማስን ለመደምሰስ እና ዋሻዎችን ለማፍራረስ ከአሜሪካ ጋር የተቀናጀ እርምጃ እንዲሰወድ መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ እንደተናገሩት፤ በእስራኤል ቁጥጥር ስር ባለው የጋዛ ክፍል ላይ የተጀመረው የተኩስ አቁም እና የእስረኞች ልውውጥ ስምምነት እንደተጠበቀ ቢሆንም፤ የቡድኑን ሰራዊት ማፍረሱ እንዲቀጥል መመሪያ መስጠቱን አስታውቀዋል።

የእስራኤል ጦር፤ የእስራኤላዊያንን ደህንነት ከመጠበቅ ጎን ለጎን የሃማስ ዋሻዎችንም ማውደም ይቀጥላል ማለታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ እና ሃማስን ትጥቅ ከማስፈታት ጎን ለጎን በቀሪው ግዛት ውስጥ የሚገኙትን የአሸባሪዎች ዋሻ ሙሉ ለሙሉ መውደም እንደሚገባው መግባባት ላይ ተደርሷል ሲሉም ካትዝ ተናግረዋል።

10 ሺሕ የሚጠጉ የዩክሬን ወታደሮች በሩሲያ ጦር መከበባቸውን ፑቲን ተናገሩ

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ከ10 ሺሕ የሚጠጉ የዩክሬን ወታደሮች በሩሲያ ጦር ተከበዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ፑቲን የሩሲያን ኮማንድ ፖስት በትላንትናው እለት እየጎበኙ ባሉበት ወቅት፤ ወደ 10 ሺሕ የሚጠጉ የዩክሬን ወታደሮች በኩፕያንስክ እና በክራስኖ አርሜይስክ አካባቢዎች በሩሲያ ጦር መከበባቸውን አስታውቀዋል።

ፑቲን አክለውም 31 የሻለቃ ማዕረግ ያላቸው የዩክሬን ወታደሮች ለሩሲያ ጦር እጅ ሰጥተዋል ሲሉ አክለዋል፡፡

ፑቲን የተከበቡትን የዩክሬን ወታደሮች እጅ እንዲሰጡ በማድረግ፤ ጉዳቱን መቀነስ የሚያስችል ጥንቃቄ የተሞላበት ወታደራዊ ኦፕሬሽን እንዲደረግም ማዘዛቸውን አርቲ ኒውስ ዘግቧል።

የሩስያ ጦር ለጠላቶቹ ምንጊዜም ምሕረትን እንደሚያደርግ የጠቆሙት ፑቲን፤ ይህ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።


#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ