መስከረም 13/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎በአዲሱ የቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥር መመሪያ (ማሻሻያ) መሠረት የቡና ላኪነት የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ለማግኘት የሚጠየቀው የ20 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል፤ መካከለኛ ባለሃብቶች ወደ ዘርፉ እንዳይገቡ እያደረገ ነው ሲል የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር አስታውቋል።

የቡና ምርት ከወቅቱ የቡና ግብይት ሁኔታ ጋር የሚሄድ ባለመሆኑ አዲሱ መመሪያ፤ ወደ ዘርፉ ለመግባት የሚፈልጉ ባለ ሀብቶች እንዳይገቡ እንቅፋት እንደሚሆን ነው ማህበሩ የገለጸው፡፡

የማህበሩ የመምሪያ ኃላፊ ገብረመስቀል ሀይሌ አዲሱ መመሪያ በዘርፉ አቅም የሌላቸውን ባለ ሀብቶችን ከዘርፉ የሚያወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

እውቀት ያላቸው እና ሥራውን የሚያውቁ ግለሰቦች ከዘርፉ እንዲወጡ የሚያደርግ መመሪያ መሆኑን ገልጸው፤ በዘርፉ የሚሳተፉት የተወሰኑ ባለሀብቶች ብቻ እንዲሆኑ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ይህን የተሻሻለውን መመሪያ ማውጣት ያስፈለገው በቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥር ላይ ቡና ላኪዎችን በተመለከተ ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል ድንጋጌ በተሟላ መልኩ ባለማካተቱ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

እንዲሁም የቡና ላኪነት መነሻ ካፒታል መጠን ከወቅቱ የቡና ግብይት ሁኔታ ጋር የሚሄድ ባለመሆኑ፤ የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀትን በመጠቀም የሚፈፀሙ ሕገ-ወጥ ተግባራትን የበለጠ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲያስችል መመሪያውን ማሻሻል ማስፈለጉን ተመላክቷል።

በተጨማሪም ማንኛውም የውጪ ቡና ላኪ ከአርሶ አደር ላኪ በስተቀር ቢያንስ መሰረታዊ የቡና ጥራት ምርመራ ሊያከናውን የሚችልበት በባለስልጣኑ ብቃቱ የተረጋገጠ የቡና ላቦራቶሪ ሊኖረው እንደሚገባ ባለስልጣኑ ማሳሰቡ ይታወቃል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ