ጥቅምት 4/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል በተለይም በኢሮብ፣ ዛላንበሳ፣ አዲግራት እና ጉሎ መከዳ የሚገኙ ዜጎች ለአስከፊና ከፍተኛ የሥነ ልቦና ቀውስ መዳረጋቸውን የአውሮፓ ህብረት ከሲ ኤስ ቲ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ባደረገው የድህረ ጦርነት ጥናት መረጋገጡ ተገልጿል፡፡
ይህም ጥናት "የሰላም ግንባታ እና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን እንዴት ማሳደግ ይቻላል" በሚል ሃሳብ፤ በአውሮፓ ህብረት ትረስት ፈንድ እና በሲ ኤስ ቲ ኢትዮጵያ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በመቀሌ እና በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች የተከናወነ መሆኑ ተነግሯል፡፡

በዚህም በአካባቢዎቹ የሚገኙ ዜጎች በተለይም ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች እና ተፈናቃዮች በጦርነት፣ በሥራ አጥነት እና በመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያት ለከፍተኛ ጭንቀት፣ ድብርት እና የስነ ልቦናዊ ቀውስ መዳረጋቸውን የጥናት ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።
በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች ከፌደራል መንግሥቱ እና ከህወሓት ጦርነት አስቀድሞ ባለፋት ዓመታት የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የተካሄደባቸው በመሆናቸው፤ ለተደጋጋሚ የስነ ልቦና ቀውስ የተዳረጉ መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡
ጥናቱ ደካማ አስተዳደር፣ ሙስና፣ የወጣቶች ሥራ አጥነት፣ ፍትሃዊ ያልሆነ የሰብአዊ እርዳታ ስርጭት፣ የተፈጥሮ ሃብት ለመቀራመት የሚደረግ ጥረት እና ግልጽ የሆነ የአካባቢ አመራር አለመኖር በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ጫና በከፍተኛ ሁኔታ እያባባሰው መምጣቱን አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪዎች የሚያሰራጯቸው ከፋፋይ ትርክሮች እና ፖለቲከኞች ስልጣንን ለመቆጣጠር እና የተፈጥሮ ሃብት መቀራመት የሚያደርጓቸው ጥረቶች፤ በአካባቢዎቹ ውጥረቶችን እና አለመግባባቶች እንዲባባሱ ምክንያት ሆኗል ተብሏል፡፡

እነዚህም በአካባቢዎቹ ዜጎች ላይ የተስተዋሉ ችግሮች ለመፍታት ጥናት ማካሄድ ብቻ በቂ አለመሆኑ የተገለጸም ሲሆን፤ በአውሮፓ ህብረት ትረስት ፈንድ እና በሲ ኤስ ቲ ኢትዮጵያ ድጋፍ የሚደረግለት ፕሮጀክት ተግባራዊ በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
በዚህም መሠረት ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የ5 ነጥብ 8 ሚሊየን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ "መረጋጋት እና ማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ልማት" የተሰኘ ፕሮጀክት ወደ ሥራ መግባቱ ተነግሯል፡፡
በዚህም ፕሮጀክት አማካኝነት በክልሉ የሕብረተሰብ ሰላም ትስስርን ማጠናከር፣ የሥነ ልቦና ቀውስ የደረሰባቸው ዜጎች የምክር እና የሕክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ፣ በአካባቢያዊ የሰላም መዋቅሮች የሴቶችን አመራር ማጠናከር እንዲሁም፤ የፋይናንሲንግ እና የወጣቶች ሥራ ፈጠራን የማስፋፋት ሥራዎች እንደሚሰሩ ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም የአእምሮ ጤና በማሻሻል ማህበረሰባዊ ትስስርን የማጠናከር፣ ከስነ ልቦና ድጋፍ ጎን ለጎን ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ የማድረግ እና በግጭት የተጎዱ ማህበረሰቦችን ከማገገም ወደ ቀደመ ሕይወት እንዲሸጋገሩ መርዳት ላይ በፕሮጀክቱ ትኩረት ተሠጥቶ እንደሚሰራ ተጠቁሟል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ