መስከረም 23/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎በአማራ ክልል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች አሁንም ወደትምህርት ገበታቸው መመለስ አለመቻላቸውን ተከትሎ ለችግሩ መፍትሄ ለማምጣት የትምህርት ሚኒስቴር፣ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር)፤ በ2018 የትምህርት ዘመን እስከ መስከረም 20 በተደረገው የምዝገባ ሂደት ከ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ልጆች እስካሁንም ድረስ መመዝገብ አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

Post image

እስካሁን ምዝገባ ያከናወኑ ተማሪዎች 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውን የሚገልጹት ኃላፊው፤ ይህም ይመዘገባሉ ተብሎ ከታቀደው 46 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ ከ2 ሺሕ 400 በላይ ትምህርት ቤቶች ዝግ መሆናቸውን የገለጹም ሲሆን፤ ከ1 ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ከተባለለት አላማ ውጪ ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ልጆች የሥነ-ልቦና ጥቃትን ጨምሮ በርካታ ችግሮችን እያሳለፉ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ይህም ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ ችግር አሁናዊ ግጭት፣ ጦርነት በተካሄደባቸውና ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ድርቅና የምግብ ውስንነት፣ ተፈናቃዮችና ሌሎች በክልሉ ያሉ ተደራራቢ ችግሮች መንስኤ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በ2016 የትምህርት ዘመን ከ5 ሚሊዮን 600 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ እንደነበረ ያነሱት ኃላፊው፤ ክልላዊና ሀገር አቀፍ ፈተናዎችን መውሰድ ከቻሉት ውስጥ አብዛኞቹ የማለፊያ ውጤት ማምጣት መቻላቸውን አንስተዋል።

ይህም ተማሪዎች በግጭት ውስጥ እንኳ ሆነው ለትምህርት ትልቅ ትኩረት መስጠታቸውን የሚያሳይ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ በመንግሥት በኩል በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

ከእዚህም ውስጥ ክልሉ በቢሊዮን የሚቆጠር በጀት በመመደብ መምህራንን የማብቃትና የማሰልጠን የትምህርት ግብአቶችን የማሟላት እና ባለው ነባራዊ ሁኔታ በሥራ ገበታ ላይ ለማይገኙ መምህራን ጭምር ደመወዝ መክፈል መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከሀይማኖት አባቶች ጋር፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሲቪል ማህበራትና ከማህበረሰቡ እንዲሁም፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሙሉ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

ሆኖም ግን አሁንም ድረስ ችግሩ በሚፈለገው ልክ መቀነስ ባለመቻሉ፤ ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያደርግ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው፤ በትምህርት ዘርፍ አዲስ የትምህርት ስርዓት ከመቅረፅ ጀምሮ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን አንስተው በዚህም ጥሩ ውጤት ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል።

Post image

ከዚህ በተለየ መልኩ ግን በርካታ ተግዳሮቶች መኖራቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዲኤታዋ፤ ከእነዚህም ውስጥ አንደኛው እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆችን ወደትምህርት ቤት አለመሄድ መሆኑን አንስተዋል።

ይህ ችግር በስፋት በሚስተዋልበት በአማራ ክልልም እስካሁን ድረስ በርካታ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ 'በ2018 የትምህርት ዓመት ወደ ትምህርት ይመለሳሉ' ተብሎ ከታቀደው ውስጥም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ወደ ትምህርት ገበታ መምጣት አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ልጆት ወደ ትምህርት አለመመለሳቸው ከራሳቸው ከልጆች አልፎ በክልሉና በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሁም፤ ለዓለም ትልቅ አበርክቶት የሚያደርጉ የነበሩት ሳይማሩ እንዳይቀሩ ሁሉም አካል ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

በመሆኑም ሚዲያዎች ችግሩን በጥልቀት ከማንሳት ባሻገር የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ በስፋት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተጠቁሟል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ