መስከረም 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ የመጨረሻውን ሀገራዊ የምክክር ሂደት ከመጪው የካቲት ወር በፊት እንደሚያጠናቅቅ ለአሐዱ አስታውቋል።
ይህም የምክክር ሂደት ስኬታማ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ፤ ማዕከላዊ መንግሥቱን ጨምሮ ጫካ የገቡ ታጣቂዎች የበኩላችውን ትብብር ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስቧል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ኮሚሽኑ በሀገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ ኢትዮጵያንና ትውልድ ኢትዮጵያ ጋር ጥልቅ የሆነ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
ይህን አጀንዳ ወደ አንድ በማምጣት ከመጪው የካቲት ወር 2018 ዓ.ም አስቀድሞ አጠቃላይ የሀገራዊ የምክክር ሂደት ለማድረግ መታቀዱንም ለአሐዱ ተናግረዋል።
በዚህም የምክክር ሂደቱ ጥሩና ስኬታማ እንዲሆን መንግሥት በቀዳሚነት ቁርጠኛ ይሆናል ብለን በፅኑ እናምናለን" ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በተለያዩ አካባቢዎች ነፍጥ አንግበው እየተዋጉ የሚገኙና እስካሁን ድረስ ለኮሚሽኑ አጀንዳቸውን ያላቀረቡ ታጣቂዎች ሀገርን በማስቀደም ወደ ምክክር ኮሚሽኑ እንዲቀርቡ ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል።
"እስካሁን በተካሄዱ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቶች የጸጥታ ችግር በሚታይባቸው በአማራ ክልልና በኦሮሚያ ክልል ጥሩ የሆነ አፈፃፀም ተደርጓል፤ ነገር ግን በትግራይ ክልል አሁንም አሳቻይ የሆነ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተካሄዷል ብሎ በሙሉ ልብ መናገር አይቻልም" ሲሉም ገልጸዋል። ሆኖም በክልሉ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
የሁሉም ወገን አላማ አንድ ኢትዮጵያ እስከሆነች ድረስ ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ መሳካት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚገባ ያሳሰቡት ኮሚሽነር ዮናስ፤ መንግሥትን ጨምሮ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ በትጥቅ ትግል ውስጥ ያለ አካል ትጥቁን አስቀምጦ እስከመጣ ድረስ ወደ ትግል ባስገባው አጀንዳ ላይ ጭምር ሰላማዊ ውይይት በማድረግ የመፍትሄ አካል መሆን እንደሚቻልም አስታውቀዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ኮሚሽኑ የመጨረሻውን ሀገራዊ ምክክር ሂደት ከየካቲት ወር በፊት እንደሚያጠናቅቅ አስታወቀ
