መስከረም 13/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በየዓመቱ በዓይን ሕክምና ዘርፍ የሚመረቁ ባለሙያዎች ቁጥር ከ50 እንደማይበልጥ የኢትዮጵያ ዓይነስውራን ባለሙያዎች ማኅበር አስታውቋል።
"የዓይን ሕክምና ባለሙያዎች እጥረት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል" ያለው ማኅበሩ፤ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ደረጃ በዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ከወጣው በአማካይ አንድ የዓይን ሐኪም ለ250 ሺሕ ሰዎች የሚለውን የማያሟላ መሆኑን ገልጿል፡፡
የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ኩሙሌ ቶለሳ፤ ችግሩን ካባባሱት ምክንያቶች ውስጥ የዓይን ሕክምና የሚያስተምሩ ተቋማት 7 ብቻ መሆናቸው እና ወደ ዘርፉ የሚቀላቀሉ ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን በዋነኝነት እንደሚጠቀሱ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በተለይም የዓይን ሕክምና ከከተማ በራቁ ገጠራማ አካባቢዎች ላይ በተደራጀ መልኩ ባለመስፋፋቱ ምክንያት፤ ሕብረተሰቡ በቀላሉ መዳን በሚችሉ የዓይን ሕመሞች በመሰቃየት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት የሕክምና አገልግሎቱን ማግኘት ወደሚችልባቸው አካባቢዎች ሪፌር በመደረግ፤ ለከፍተኛ ወጭና እንግልት እየተዳረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቁና በርካታ የዓይን ሕክምና ባለሙያዎች እንዲፈሩ በማድረግ፣ ለጤና ባለሙያዎች ተገቢ ሥልጠና በመስጠት እንዲሁም፤ ከከተማ በራቁ አካባቢዎች ላይ የዓይን ሕክምና ቁሳቁስና ግብዓቶችን በማሟላት ችግሩን ለመቅረፍ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ማኅበሩ ችግሩን ለመቀነስ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑን የገለጹት አቶ ኩሙሌ፤ የዓይን ሕክምና ትምህርት የሚሰጡ ተቋማትን ለማስፋፋትና ያሉትን ባለሙያዎች በቅንጅት ለማሰራት ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ250 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ለከፍተኛ የዓይነ ስውርነት አጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ