ጥቅምት 29/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የተሰጣቸውን የመንግሥትና የሕዝብ ሃላፊነት ወደ ጎን በመተው ሲቀሳቀሱ በተገኙ፤ 26 ሺሕ 68 አመራሮች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቋል።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ጫልቱ ግርማ ከአመራሮቹ በተጨማሪ 406 በሚሆኑ ባለሙያዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን የገለጹ ሲሆን፤ 405 ተቋማት ደግሞ እንዲዘጉ ተደርጓል ብለዋል።

በዚህ በሙስና እና በብልሹ አሰራር ላይ በተሳተፉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ተቋማት ላይ የተወሰደው እርምጃም፤ ከሥራ ማገድ፣ የገንዘብ ቅጣት፣ በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ እንዲሁም ተቋማቶቹን ጭራሹን መዝጋት መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ በአሰራር ስርዓቱ ላይ እያጋጠመው ያለውን እንቅፋት ለመፍታት የ7 ዓመት የሪፎርም እቅድ መንደፉን የገለጹት ኃላፊዋ፤ "መተግበር ከጀመረ ሁለት ዓመት የሞላው ይኸው ሪፎርም አዎንታዊ ለውጥ እያመጣ ነው" ብለዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ