ጥቅምት 29/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በመዲናዋ በቅርቡ ተጠግነው ወደ ሥራ የገቡትን ጨምሮ 1 ሺሕ 239 የከተማ አውቶብሶች የትራንስፖት አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት አስታውቋል።

በከተማዋ ያለውን የትራንስፖርት ፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣም ችግር ለመፍታት በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ባሉት ሦስት ወራት በብልሽት ምክንያት አገልግሎት ያቋረጡ 10 አውቶብሶች ተጠግነው ወደ ሥራ ተመልሰዋል ተብሏል።

የተቋሙ የአገልግሎት ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ከበደ፤ በተለይም ረዥም ርቀት የሚጓዙ ዜጎች ሰልፍ ላይ የሚያጠፉትን ሰዓት ለመቀነስ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የከተማ አውቶብሶችን ቁጥር የመጨመር እንዲሁም፤ በብልሽት ምክንያት አገልግሎት ያቋረጡ አውቶብሶችን ጠግኖ ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አክለውም፤ "በብልሽት ምክንያት አገልግሎት ያቋረጡ አውቶብሶችን ጠግኖ ወደ ሥራ የማስገባት ሂደት ላይ ከሚያጋጥሙ ችግሮች መካከል፤ የመለዋወጫ ግብአቶች በበቂ ሁኔታ ሀገር ውስጥ አለመኖር ይገበኝበታል" ብለዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት የሚያስችሉ መለዋወጫዎች በቅርቡ ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውንና ተጨማሪ መለዋወጫዎችም በሂደት ላይ እንደሆኑ የአገልግሎት ድጋፍ ዳይሬክተሩ ለአሐዱ ራዲዮ አስታውቀዋል፡፡

የሕዝብ ማመላለሻ የአውቶብስ ተሽከርካሪዎች ዕለታዊ ፍተሻ እና ወርሃዊ የቴክኒክ ምርመራ ይደረግላቸዋል ተብሏል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ