ሕዳር 22/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ከፍተኛ የመንግሥት ሹመኞች የሚፈጽሟቸውን እንደ የሕዝብ ሀብት ምዝበራ ያሉ የሙስና ወንጀሎች ለመከላከልና ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችሉ ጠንካራ ማስረጃዎች ማግኘት ትልቁ ፈተና መሆኑን የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ገልጿል።

አንዳንድ ከፍተኛ ኃላፊዎች የመንግሥትን ፖሊሲና አሠራር በማዛባት የሕግ የበላይነትን እና የኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶችን እያሰናከሉ መሆኑን የሕግ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ቢያነሱም፤ የተጠረጠሩትን ባለስልጣናት ፍርድ ቤት ለማቅረብ የሚያስችል ማስረጃ ማግኘት ግን አስቸጋሪ ነው ተብሏል።

በኮሚሽኑ የሙስና መረጃዎች አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን በላይነህ፤ "በተቋማት አመራሮች አማካኝነት የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከልና ጥፋት ፈጻሚዎችን ለማስቀጣት ከወሬ የዘለለ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን ማግኘት አስቸጋሪ ነው፤ ተጨባጭ ማስረጃ ሳይገኝ ደግሞ አንድን ግለሰብ የሕግ ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም" ሲሉ ለአሐዱ ሬዲዮ ተናግረዋል።

"ሙስና በፈጻሚዎቹ ስልጣን እና ኃላፊነት እንዲሁም በዓይነቱ በ4 ደረጃዎች አሉት" በማለት ያብራሩት አቶ መስፍን፤ በከፍተኛ ሹማምንት የሚፈጸመውን መጠነ ሰፊ፣ በታችኛው መዋቅር ሹመኞች የሚፈጸመውን ጥቃቅን፣ በፖለቲካዊ ውሳኔ የሚፈጸመውን የፖለቲካ፣ ሕጋዊ መንገድን በተከተለ የሕግ ክፍተት የሚፈጸመውን ስርአታዊ በማለት ከፋፍለው አቅርበውታል።

ሥራ አስፈጻሚው በመጨረሻም፤ "እስካሁን ለፈጸመው የሕዝብ እና መንግሥት ንብረት ምዝበራ ሙስና ወንጀል ማስረጃ ተገኝቶበት በሕግ ተጠያቂ ያልሆነ የመንግሥት ኃላፊ የለም" ብለዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ