ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመደመር መንግሥት ዕይታ የዘርፎች እመርታ በሚል ርዕስ ለብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሰጡት ስልጠና ላይ ባደረጉት ገለፃ፤ "ችግር ጠልፎ የሚጥለን ሳይሆን ገፍቶ የሚያስፈነጥረን መሆን አለበት" ብለዋል፡፡
በስልጠናው ወቅት በርካታ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በርካታ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የሲቪክ ባህልን በማጎልበት በስምምነት እና በመግባባት የጋራ አስታራቂ ተቋማት እና ሕጎች መፍጠር ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ያለፈውን ትውልድ ስህተት ማስተካከል፣ ማስፋት እና ማበርከት የመደመር ትውልድ ግንባታ መርሆዎች ናቸው ብለዋል፡፡
ኢኮኖሚን በተመለከተ በቅድሚያ ያነሱት መዋቅራዊ እና ሰው ወለድ ጭቆና መወገድ አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሲቪክ ባህል መዳበር አለበት ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ይሁንና "አሁንም ተቃርኖዎች አሉ" ያሉም ሲሆን፤ "ኦሮሚያ በእርሻ አድጓል አዲስ አበባ ሪቨር ሳይድ ለምቷል እየተባለ ወደ ሌሎች ማተኮር አለ" ብለዋል፡፡
"ነገር ግን እንደ አዲስ አበባም ሆነ እንደ ኦሮሚያ መልማት የከለከለ ክልል የለም" ሲሉም፤ ይህንን ጥያቄ ለሚያነሱ አመራርሮች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ሁለተናዊ ልማት የሚፈለግ ከሆነ ለሁሉም ያስፈልጋል ግን ከሁሉም ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ያለባት ሀገር ካልሆነች በቀር ሰላማዊ እና ልማታዊ ጉዞ ማድረግ እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡
ለዚህም አስተዳደሩ እውነተኛ ፌዴራሊዝም የሚተገብር፣ ብዝኃ ቋንቋን የሚጠቀም፣ ብዝኃ ማንነትን የሚያቅፍ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

የወንድማማችነት እሴትን ማጽናት የመደመር ትውልድን ቁልፍ ጥያቄዎችን ለመመለስ ዋነኛው መንገድ እንደሆነ አንስተው፤ ብሔርን እና ሀገራዊ ብሔርተኝነትን ማስታረቅ እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡
መደመራዊ ዝላይ የሚያስፈልገው ክፍተትን ለመሙላት እንደሆነ ጠቅሰው፤ "እመርታ ከዝላይ ውጪ ሊመጣ አይችልም የሚል እሳቤ በውስጡ አለው" ሲሉ አስረድተዋል፡፡
"በእመርታ ድልድይ መገንባት መዳረሻው ሁለንተናዊ ብልጽግና ነው" በማለት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሁለንተናዊ ብልጽግና ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ሁሉን ነገር በውስጡ ያሟላ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡
ሁለንተናዊ ብልጽግና ሁለንተናዊ ትጋትና ዘመን የዋጀ ብቃት ደምሮ መያዙን ገልጸው፤ "ይህ ሲሆን ግን ባህልን ያበላሸ እና ግብረ ገብን ያጠፋ መሆን የለበትም" ብለዋል፡፡
"አሻጋሪ የሆነ መንግሥት ካለንበት አረንቋ ወደ ብልፅግና የሚያሸጋግር እንዲሆን፤ የበለፀገ ማህበረሰብ ለመፈጠር ሁለት ሶስት ጉዳዮችን መመለከት ያስፈልጋል" ሲሉም ገልጸዋል፡፡
መንግሥት፣ ገበያ እና ማህበረሰብ ሁልጊዜ ርዕዮተዓለሞች በነዚህ ዙሪያ ላይ የሚያነጣጥሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከከፍተኛ አመራሮች ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ስለ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መንግሥት እሳቤም አንስተው ሀሳብ ሰጥተውበታል፡፡
"አብዮታዊ ዲሞክራሲ መንግሥት ተራማጅ የፖለቲካ ልሂቃንና የኢኮኖሚ ሊሂቃንን በእኩል አይን አያይም" ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ቀጥለውም "ተራማጅ የፖለቲካ ልሂቃን ለሕዝብ አሳቢ እራሳቸውን እንደ ሻማ አቅልጠው ለሕዝብ የሚሰሩ ናቸው ቢልም እንደምታወቁት አብዛኞች በወቅቱ የነበሩ ፖለቲከኞች ግን ዘራፊ ነበሩ" ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
በመሆኑም የመደመር መንግሥት የነጠረ የመንግሥት ሚና የሚጫወትበት ከግል ሴክተር፣ ከሕዝብ እንዲሁም ከአጋር ድርጅቶች ጋር ተቀነጅቶ የሚሰራበት የመደመር መንግሥት ፈጠራና ፍጥነት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ግብርናውንም በሚመለከለት ከተረጂነት መውጣት እና የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ ስለመሆኑም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናግረዋል፡፡
ወደ አምራችነት ለመሄድ ሙከራዎች መኖራቸውን ያነሱ ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ የገጠር ሽግግር ላይ መስራት አለብን ብለዋል፡፡
በተለይም ከነፍስ ወከፍ ወደ ገበያ የሚቀርብ መሆን አለበት ያሉም ሲሆን፤ በዋናነትም ከዕለት ጉርስ ግብርናውን ወደ ገበያ እንቀይረው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ማዳበሪያ መጠቀም፣ ምርጥ ዘር መጠቀም እንዲሁም፤ ኩታ ገጠምና ማሽን መጠቀም መለማመድ አለብን ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ከቅርስ ጋር በተያያዘም ሰፋ ያለ ሀሳብ የሰጡ ሲሆን፤ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ 10 ሺሕ የሳዑዲ ዜጎች ወንጪን መጎብኘታቸውን ለአመራሩ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ "ትላልቅ ቅርስ ይዘን ወደ ቁርሰ መቀየር አልቻልንም" ያሉም ሲሆን፤ የገንዘብ ምንጭ መሆን የሚችሉ ቅርሶች መጠገን በማይቻልበት ደረጃ ላይ ወርደዋል ብለዋል፡፡
ቅርሶች ወደ ገንዘብ ለመቀየር ደግሞ ቅርሰ ብቻ መኖሩ በቂ ባለመሆኑ፤ ለዚህ የሚሆን አገልግሎት እና ሰላም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
"አሁን ላይ በርከታ መስዕቦች ቢኖሩንም ማረፊያዎች የሉንም ይህንን ማድረግ ካልቻልን ውጤት ማምጣት አይቻልም" ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
በማጠቃላያቸውን "የሚቀጥሉት አምስት ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያን ሌላ ምዕራፍ ላይ ማድረስ ይቻላል" ብለዋል፡፡
ይህንን የኢትዮጵያ ብልፅግና እውን ለማድረግ በርክት ያሉ አቅጣጫዎችን ያስቀመጡ ሲሆን፤ "የመጀመሪያው ሉዓላዊነት ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡ "የምግብ ልዑዓላዊነት እና የሀሳብ ልዑላዊነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን መሠራት ያስፈልጋል" ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸዋል፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ተጀመሩ ሥራዎችን ማስቀጠል መሆኑን ገልፀው፤ በሦስተኝነት ደረጃ አገልግሎቶችን ማዘመን እና ምቹ ማድረግ ያስፍልጋል ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
ሌላው ለምርጫ አስቻይ ሁኔታ መፍጠር መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "እነዚህ ማሳካት ይገባል" ብለዋል፡፡
"በልበ ሙሉነት ሥራዎቻቹን መሠራት ከቻላችሁ በ2036 ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚውን ኢኮኖሚ ትይዛለች" ሲሉ፤ ለከፍተኛ አመራሮቹ ገልጸዋል፡፡
ብረት ከወጣ፣ ጋዝ ከወጣ ፣ኢንዱስትሪዎች ከተስፋፉ እና ሁሉም የሚለፋ ከሆነ ኢትየፐጵያ የድህነት ታሪኳ ይቋጫል ብለዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ