ሕዳር 22/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ዜጎች በብሔራዊ ጥቅም ላይ የጋራ መግባባት እንዲኖራቸው ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር የጋራ ትርክት ለመገንባት በስፋት እየሰራ እንደሆነ ሰላም ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ በዋነኝነት ትኩረት የሚያደርገው ማኅበራዊ ትስስር በመፍጠርና ዜጎች በሀገራቸው ላይ እምነት እንዲኖራቸው በማድረግ ላይ እንደሆነም፤ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ሚንስትሩ ይህን የገለጹት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ከምርጫ ዘገባ ጋር በተገናኘ ስልጠና በሚሰጥበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡

ዶ/ር ከይረዲን ሚኒስቴሩ በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 እንደገና መቋቋሙን አስታውሰው፤ ብዙ ሰዎች ተቋሙን "የፀጥታ ተቋም" አድርገው እንደሚገምቱት ገልጸዋል።

ሆኖም የተቋሙ ዋና ተግባር ዜጎች ስለኢትዮጵያ ያለፈ ታሪክ፣ ዛሬ ስላለችበት ሁኔታ እና በቀጣይ ምን እንደሚያስፈልጋት ተቀራራቢ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ፤ 'ብሔራዊ ጥቅማችንና የጋራ እሴቶቻችን ምንድን ናቸው?' በሚሉት ሐሳቦች ዙሪያ የጋራ መግባባት መፍጠር ነው ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ይህን የጋራ ትርክት የማፍራት ዓላማ ለማሳካት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ዶክተር ከይረዲን አስታውቋል።

"ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በሚኖር የሕብረት ሥራ ደግሞ፤ የታሪክ፣ የባህል፣ የማንነት እና የሀገር ግንባታ ጉዳዮች ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ በተቀናጀ መልኩ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ እንዲካተቱ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ሰላም ሚኒስቴር ብሔራዊ መግባባት የማምጣት ሐሳቡን ለማሳካት፤ ከመንግሥት፣ ከግልና ከሐይማኖት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከምሁራን እና ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሀገር ጉዳይ ላይ የጋራ ትርክት ለመፍጠር ያለመ ውይይቶች ማድረጉን አስታውሰዋል።


#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ