ሕዳር 16/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል በጅማ ክላስተር እና በአራቱ የወለጋ ዞኖች ከሚገኙ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ጋር ውይይት ማድረጉን ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ በጅማና በወለጋ አራቱ ዞኖች የሚገኙ ወጣቶችን፣ አካል ጉዳተኞችና ሴቶችን በማወያየት፤ በቀጣይ ለሚያከናውነው ተግባር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መስራቱን ገልጿል፡፡

Post image

የኮሚሽኑ የተደራሽነት እና አጋርነት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ፍሬ ስናይ ገበየሁ ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በሀገሪቱ ላጋጠሙ ችግሮች ወሳኝ የሆኑ የመፍትሔ ሀሳቦች እንዲቀርቡ ተሳታፊዎችን ጠይቋል።

በምክክር ሂደቱ የወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም አካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና እስከ ታችኛው ማህበረሰብ እንዲወርድ ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች መነሳታቸውን ገልጸዋል።

Post image

በሀገሪቱ ቀደም ብሎ ላጋጠሙ ችግሮች ዘለቄታዊ መፍትሔ ለመስጠት የሀገራዊ ምክክር ሂደት ወሳኝ ሚና እንዳለው ተወያዮች ማንሳታቸውን እና ያነሱትን ሀሳብም በቀጣይ ለሚካሄደው ጉባኤ ግብዓት በመሆን እንደሚያገለግል ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል በተደረገው መድረክ 6 መቶ ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም አካል ጉዳተኞች መሳተፋቸውን አንስተው፤ "ተወያዮች በሚፈጠሩ አለመግባባቶች በዋናነት ተጎጂ የሆኑት ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም አካል ጉዳተኞች በመሆናቸው የሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች በውይይት መፈታት እንዳለባቸው ጠይቀዋል" ብለዋል።

በክልሉ የሚገኙ ወጣቶች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መሆናቸውን የገለጹት ከፍተኛ ባለሙያው፤ በምክክር ሂደቱ በመሳተፍ የመሪነት ሚና መጫወት እንዳለባቸው አፅንዖንት መስጠታቸውን ለዚህም ኮሚሽኑ ምቹ ሁኔታን መፍጠር አለበት ሲሉ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውቀዋል።

Post image

ኮሚሽኑ ከኦሮሚያ ክልል በተጨማሪ በአፋር ክልል ተመሳሳይ መድረክ በማካሄድ በቀጣይ ለሚደረገው የምክክር ሂደት ግብዓት ማሰባሰቡን የተናገሩት የኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለሙያ፤ በቀጣይም ተመሳሳይ የመድረክ በጋምቤላ ክልል እንደሚያዘጋጅ ጠቁመዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ