ሕዳር 17/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትግራይ ክልል የሚገኙ አካል ጉዳተኞችን፣ ወጣቶችንና ሴቶችን በቀረው አጭር ጊዜ ውስጥ በተለየ ሁኔታ ለማወያየት እና ግንዛቤ ለማስጨበጥ የቅድመ ዝግጅት ሥራውን ማጠናቀቁን አስታውቋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የተደራሽነት እና አጋርነት ከፍተኛ ባለሙያ ፍሬ ስናይ ገበየሁ ለአሐዱ ሬዲዮ እንደተናገሩት፤ በትግራይ ክልል ምክክር ለማድረግ ከጊዜያዊ አስተዳደሩና በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ማህበራት ጋር በመቀራረብ እየተሰራ ነው፡፡ በክልሉ ምክክር ለማድረግ ፍላጎት መኖሩንም ተናግረዋል።

በዚህም ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በቀሩት ጊዜያት ውስጥ የክልሉን ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ሴቶች የማወያየትና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በቅርቡ ይሰራል ሲሉ ገልጸዋል።
በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የሲቪክ ማህበራትና የመገናኛ ብዙኃን አካላት ጋር በመተባበር አካል ጉዳተኞችን፣ ወጣቶችንና ሴቶችን ለማወያየት የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን ጠቁመዋል።
ከዚህ በፊት ከትግራይ ፖለቲከኞች፣ ሲቪክ ማህበራት እና ከሊህቃን ጋር የተደረጉ ውይይቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ከፍተኛ ባለሙያው፤ በዚህ የውይይት መድረክ በክልሉ የሚቀሳቀሱ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች መሳተፋቸውን አስታውሰዋል፡፡
ኮሚሽኑ ቀጣዩን ውይይት በክልሉ ለማድረግ ሁኔታዎች እንደተመቻቹ ቀኑን እንደሚያሳውቅ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማድረግም ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም፤ ከክልሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር በመስራት ከአካል ጉዳተኞችና ወጣቶች እንዲሁም ሴቶች ጋር ውጤታማ ውይይት ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ለአሐዱ ገልጸዋል።
በህይወቴ ጌትነት
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ