የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የማርበርግ ቫይረስን ስርጭት እና ያስከተለውን ጉዳት በተመለከተ ወቅታዊ መረጃ የያዘ ጋዜጣዊ መግለጫ በዛሬው ዕለት ሰጥተዋል።
ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የማርበርግ ቫይረስ በሽታ መከሰቱ በላቦራቶሪ ምርመራ መረጋገጡን አስታውሰዋል። እስከአሁን 73 የተጠረጠሩ ሰዎች ላይ ምርመራ መደረጉን ገልጸዋል።

ከእነዚህም ውስጥ 6 ታማሚዎች ሕይወታቸው በቫይረሱ ያለፈ መሆኑ በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሪፈረንስ ላቦራቶሪ እንዳረጋገጠ በዛሬው መግለጫ ላይ ተነሥቷል።
በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠ ሰዎች መካከል አምስት የሚሆኑት ሕክምና እየተደረገላቸው ይገኛል።
እስካሁን 349 ሰዎች ቫይረሱ ካለበት ሰው ጋር ንክኪ እንዳላቸው በመጠርጠሩ ክትትል እየተደረባቸው ይገኛል ተብሏል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 119ኙ የለይቶ ማቆያ ጊዜያቸውን ማጠናቀቃቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የለይቶ ማከሚያ ማዕከላትን የማቋቋም፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል የማደራጀት እና አስፈላጊ የሕክምና ግብዓት የማቅረብ ሥራ መሠራቱን ዶክተር መቅደስ ዳባ ተናግረዋል።

ለታማሚዎች የተጠናከረ የሕክምና እርዳታ እንደተሰጠ፣ የተሻለ ሕክምና ለመስጠት እንዲቻል ከዚህ በፊት ወረርሽኙ ተከስቶባቸው ከነበሩ ሀገራት ጋር የልምድ ልውውጥ መደረጉም ተገልጿል።
ልምድ በመቅሰም ጥሩ ውጤት ያስገኙ መድኃኒቶችንና ክትባቶችን በመለየት ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለታካሚዎች ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
በዛሬው መግለጫ በቫይረሱ እስከ ዛሬ ጠዋት በተደረገ ምርመራ 11 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን፤ 6 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው ማለፉን ሚኒስትሯ ተናግረዋል። የላብራቶሪ ምርመራውም እስከ ትላንት በነበረው መረጃ 71 የነበረው ቁጥር ከፍ ብሎ 73 ደርሷል፡፡ የሟቾች ቁጥርም ወደ 6 ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የማርበርግ ቫይረስ ከሚያጠቃቸው ሰዎች መካከል በአማካይ ግማሹን ለሞት እንደሚዳርግ ይገልጻል። ቀደም ሲል በተከሰቱት የበሽታው ወረርሽኞች ከተያዙት መካከል ከ24 እስከ 88 በመቶ የሚሆኑትን ታካሚዎች ለሞት እንዳደረገ መረጃው ያሳያል።
ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው በአውሮፓውያኑ 1967 በጀርመን ማርበርግ እና ፍራንክፈርት እንዲሁም በሰርቢያ ቤልግሬድ በተከሰቱት ወረርሽኞች ነው። በወቅቱ 31 ሰዎች በቫይረሱ ከተያዙ በኋላ ሰባቱ በበሽታው ምክንያት ለህልፈት ተዳርገው ነበር።
በኢትዮጵያ የተከሰተውን ይህንን ቫይረስ አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ለሁለተኛ ጊዜ መግለጫ የሰጡት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የነበራቸውን ወደ 349 ሰዎች ክትትል ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ ወደ 119 የሚሆኑት የክትትል ጊዜ ገደባቸውን ጨርሰው ከለይቶ ማቆያው መውጣታቸውን ገልጸዋል።
አዲስ የሚያዙ ሰዎች ከተገኙ የለይቶ ማቆያ ማዕከላት፣ የሕክምና አቅርቦቶች እና የሰለጠኑ ሠራተኞች ዝግጁ መሆናቸውን ያረጋገጡት ደግሞ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ ናቸው።

ቫይረሱ ባልተገኘባቸው ክልሎችም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ በድንበር ቦታዎች እና በሌሎች የመግቢያ እና መውጫ ቦታዎች ላይም ምርመራው መጠናከሩን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ሕዝብ በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች፣ በተለይም በሽታው በተገኘባቸው አካባቢዎች ላይ ካርታ በመሥራት የመከታተል ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። የግንኙነት እና የትራንስፖርት አውታሮች ላይ የበሽታውን ምልክት የሚያሳዩ ሰዎችን የሚለዩ ባለሙያዎችን ማሰማራት መቻሉንም አብራርተዋል።
በበሽታው የተያዙ ግለሰቦች እስካሁን ባለው በላብራቶሪ የተረጋገጡ 11 ሰዎች መሆናቸውንም ዶክተር መሳይ ተናግረዋል።
እስካሁን ሲመረመር የቆየው አጠራጣሪ እና ንክኪ ያላቸውን ሰዎች መሆኑን የተናገሩ ሲሆን አሁን ደግሞ በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ የምርመራ ሁኔታውን እንደሚያሰፉት ገልጸዋል።
ሥራውን ዓለም አቀፍ መመሪያዎችን በመከተል እየሠሩ እንደሚገኝ የገለፁ ሲሆን፣ ዝግጅቱ ብሔራዊ መመሪያ እስከማዘጋጀት የደረሰ እንደሆነም ዶክተር መሳይ ኃይሉ አስረድተዋል።
እንደ ጤና ባለሙያዎች ከሆነ ቫይረሱ በቅርብ ጊዜ የተከሰተው በሩዋንዳ ውስጥ በመስከረም 2024 መጨረሻ ላይ መሆኑ ተገልጿል። ቫይረሱ በሩዋንዳ ሲገኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፤ ምንጩ እስከአሁን አለመታወቁ ተነግሯል። የሩዋንዳ ጎረቤት የሆኑት ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ በ2017 እና 2023 የማርበርግ ወረርሽኝ እንደተገኘ ሪፖርት አድርገው ነበር።
ይህንን ቫይረስ ለመቆጣጠር ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገልጸዋል። በዋናነት አሁን ክትትል ማድረጉ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ዶክተር መቅደስ፣ አሁን የላብራቶሪ ሥራ በስፋት እንደሚሠራ ተናግረዋል።

የድንበር ዘለል በሽታዎች እንዳይፈጠሩ ለመከላከል በድንበር ዘለል በሽታዎች ላይ የሚሠሩ ተቋማትን የማስተሳሰር ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
ይህ አሠራር ድሮም የነበረ ቢሆንም አሁን አጠናክሮ የመሥራት ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል። ይህ አካሄድ ከዚህ ቀደምም የነበረ ቢሆንም እንደዚህ ዓይነት ወረርሽኞች ሲከሰቱ በስፋት እንደሚሠራበት ተናግረዋል።
"ሕብረተሰቡን ከሐሰተኛ መረጃ መጠበቅ ያስፈልጋል" ያሉት ዶክተር መቅደስ፤ ከመደናገጥ ይልቅ መተባበር ላይ ትኩረት ተደርጎ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። በተጨማሪም ይህንን በሽታ በተመለከተ በየሳምንቱ እና በየጊዜው መረጃዎችን እንደሚያደርሱ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ