መስከረም 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ የቡና መገኛና አምራች ሀገር እንደመሆኗ በዘርፍ የሚጠበቀውን ያህል ተጠቃሚ እንድትሆን፤ ቡናን እሴት በመጨመር ለዓለም ገበያ ማቅረብ ይጠበቅባታል ሲሉ በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡

ሀገሪቱ ከቡናው ዘርፍ ልታገኘው የሚገባው ከፍተኛ ተጠቃሚነት እንዲቀንስ አድርገዋል ተብለው እንደ ምክንያት የሚጠቀሱ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም፤ ጥሬ ቡናን ብቻ ወደ ውጪ ሀገራት መላክ አንዱ የተጠቃሚነት መጠንን የሚቀንስ ምክንያት መሆኑ በተደጋጋሚ ይነሳል።

የኦሮሚያ ቡና አቅራቢዎችን ላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ፈጠነ የኋላሸት፤ የኢትዮጵያን ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊነቱ ለመጨመር የመንግሥትና የባለድርሻ አካላት ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።

በመንግሥት በኩል የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ ከሆኑ ሀገራት ጋር ጥሩ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማዳበር እንደሚጠበቅ የገለጹ ሲሆን፤ ኤምባሲዎች እና አየር መንገዶች ላይ ቡናን ለማስተዋወቅ በመንግሥት አቅጣጫ ማስቀመጥ አማራጭ መሆኑ ጠቁመዋል።

አክለውም "ኢትዮጵያ ጥሬ ቡናን የምትልክ በመሆኗ ተቀባይ ሀገራቱ እሴት ጨምሮ ለገበያ ያቀርቡታል" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ኢትዮጵያ በራሷ እሴት መጨመር ማለትም ቡናን ቆልቶ እና ፈጭቶ መላክ መጀመር እንዳለባት አንስተዋል።

"ይህ ሲሆን ግን ሀገራቱ የለመዱትን አካሄድ ለመስበር ጠንካር ዲፕሎማሲ ያስፈልጋል፡፡ የእነርሱን ጫና ብቻ መቀበል አስፈላጊ አይደለም" ሲሉም ተናግረዋል።

በተጨማሪም የንግዱ ማህበረሰብ ተወዳዳሪነቱን ማስፋት፣ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ማምረት እና በሚፈለገው መጠን መላክ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ለዚህም አምራቹ ቡናን ከሚያለማበት ወቅት ጀምሮ እስከሚሰበሰብበት ድረስ ደረጃውና ጥራቱን እንዲጠብቅ አቅሙን ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

ይህን ሃሳብ የሚጋሩት የቢዝነስና ኢንቨስትመንት አማካሪ ከፈለኝ ሃይሉ በበሉላቸው "በኢትዮጵያ አሁንም ቡና ጥሬ እንዲላክ ነው ፍላጎት ያለው" ያሉ ሲሆን፤ እሴት ጨምሮ መላክ አስፈላጊ መሆኑን ለአሐዱ ገልጸዋል።

እንዲሁም ቡናን ከቱሪዝም ጋር በማገናኘትና የቡና ፌስቲቫሎችን በማዘጋጀት ብቻ፤ ወደ ውጪ ሳይላክ እስከ 7 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘት የሚቻልበት መሆኑን አንስተዋል።

ከሦስት ዓመት በፊት የቡናና ሻይ ልማት ቡናን በሀገር ውስጥ እሴት ጨምሮ በዶላር ለመሸጥ መመሪያ አዘጋጅቶ እንደነበር፤ ነገር ግን ሳይጸድቅ መቅረቱን አማካሪው አስታውሰዋል።

ቡና ላይ እሴት ጨምሮ መላክ ገቢን የሚጨምር፣ በንግድ ሰንሰለት ውስጥ ተፈላጊነት ከፍ የሚያደርግና ጥሬ ቡና ከመላክ እሴት ጨምሮ መላክ ተወዳዳሪነት የሚጨምር መሆኑን ባለድርሻ አካላቱ ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ