መስከረም 16/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የጋምቤላ ክልል የመስቀል ደመራ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ128 የህግ ታራሚዎች ሙሉ ይቅርታ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ወ/ሮ ዓለሚቱ ኡሞድ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ታራሚዎቹ በቆይታቸው መታረማቸውን፣ መታነፃቸውን እና መጸጸታቸውን በመገንዝብ በይቅርታ እንዲወጡ ተደርጓል ብለዋል።

ታራሚዎች ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ መልካም ሥነ-ምግባር በመላበስ ለዘላቂ ሰላም እና ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ሕብረተሰቡ ይቅርታ ለተደረገላቸው ታራሚዎች ወገናዊ አቀባበል በማድረግ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው ራሳቸውንና አካባቢያቸውን እንዲለውጡ ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዶል ኡኮሪ በበኩላቸው፤ የሕግ ታራሚዎቹ የይቅርታ አዋጁን መስፈርት አሟልተው የተገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች በድርጊታቸው የታረሙ፣ የተጸጸቱና የበደሉትን ሕዝብ እና መንግሥት ለመካስ ዝግጁ እንደሆኑ መረጋገጡንም አስረድተዋል፡፡

በዚህም መሠረት በክልሉ ከሚገኙ አራት ማረሚያ ቤቶች ለ128 የሕግ ታራሚዎች ሙሉ ይቅርታ መደረጉን ጠቅሰው፣ ከነዚህም ውስጥ አራቱ ሴቶች መሆናቸውን ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ