መስከረም 16/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሜትሮዮሎጂ ኢንስቲትዩት በመጪዎቹ ቀናት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ እንደሚኖርና ይህም ለከፍተኛና ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል አስታውቋል።
ይህንን ተከትሎም "በአዲስ አበባ ያለው የአየር ሁኔታ ምን ይመስላል? ምን አይነት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው?" ሲል አሐዱ የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንን ጠይቋል።
የኮሚሽኑ የአደጋ ስጋት ጥናትና ትግበራ ዳይሬክተር ደሲሳ ጦና በምላሻቸው፤ በቀጣይ ቀናት በከተማዋ የሚኖረውን የአየር ሁኔታ አስመልክቶ ከብሔራዊ ሜትሮዮሎጂ ኢንስቲትዩት መረጃ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን የሚኖር በመሆኑ የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ ሊጨምር እንደሚችል ጠቁመዋል።
በመሆኑም የጎርፍና የመሬት መንሸራተትን ጨምሮ ሌሎች አደጋዎች እንዳይከሰቱ ሕብረተሰቡን በማስተማርና በመጠበቅ እንዲሁም፤ የአደጋ ቅነሳ ላይ ሰፊ ግንዛቤ መስጠት እንደሚያስፈልግ በመገንዘብ በዚያው ልክ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
"ከአደጋ መማር የለብንም" የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ሕብረተሰቡም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሚሰጠውን መመሪያና ቅድመ ጥንቃቄ በመቀበል ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባው ገልጸዋል።
አደጋን መቀነስ እንጂ ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት የማይቻል መሆኑን አንስተው፤ ነገርግን 'በቀጣይ ቀናት የዝናብ መጠኑን ተከትሎ ሊከሰቱ ይችላሉ' ተብለው የሚጠበቁ ድንገተኛ አደጋዎችን ለመከላከል ሰፊ ቅድመ ጥንቃቄ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በመዲናዋ በቀጣይ ቀናቶች የጎርፍና መሬት መንሸራተት አደጋዎች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ
