ለሁለት ዓመታት የቆየውን የትግራይ ጦርነት በይፋ ያስቆመው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሦስተኛ ዓመቱን አስቆጥሯል፡፡

ስምምነቱ የተደረሰው ከሦስት ዓመት በፊት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲሆን፤ በፌዴራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ለአሥር ቀናት በዘለቀ ድርድር በፊርማ መጠናቀቁ ለብዙዎች እፎይታን የሰጠ ነበር።

የሰላም ስምምነቱ ሰፋፊ ተስፋዎችን ቢሰንቅም፤ ዛሬ ላይ ቆመን ስንመለከተው አብዛኛዎቹ ቁልፍ ጉዳዮች ሳይፈቱ ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል። ከዚህም አልፎ፤ በአንድ ወቅት አጋሮች የነበሩ የህወሓት አመራሮች ተከፋፍለው የትግራይ ክልልን ወደ ዳግም ቀውስ አፋፍ እያደረሱት ይመስላል።

Post image

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በበኩላቸው፤ ያልተፈቱትን የተፈናቃዮችና የተጠያቂነት ጉዳዮችን አንስተዋል።

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የመጨረሻው ባለ 12 ነጥብ ሰነድ በዋናነት በሀገሪቱ አንድ የጦር ኃይል ብቻ እንዲኖር እና የህወሓት ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ ይደነግጋል።

ከዚህ በተጨማሪ፤ በትግራይ ክልል ምርጫ እስከሚካሄድበት ጊዜ ድረስ ሁሉን ያካተተ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚቋቋም እና በጦርነቱ ወቅት የተፈጸሙ ወንጀሎች በሽግግር ፍትሕ እንደሚታዩ ከስምምነት ላይ ተደርሷል። ከሁሉ በላይ በጦርነቱ የተፈናቀሉ ዜጎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ያስገድዳል።

ይሁን እንጂ ከሦስት ዓመታት በኋላም የስምምነቱ አብዛኛው አንቀጾች ሳይተገበሩ በመቅረታቸው፤ ክልሉ ከሁለት ዓመት አንጻራዊ ሰላም በኋላ እንደገና ወደ ግጭት መንስኤነት ለመግባት ተቃርቧል።

በግጭቱ በአንድ ወገን ሆነው ሲዋጉ የነበሩት የህወሓት አመራሮች አሁን በሁለት ጎራ ተከፍለው ተፋጠዋል። በፓርቲው ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካዔል (ዶ/ር) የሚመራው ቡድን፤ በቅርብ ወራት የወረዳና የከተማ አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶችን እየተቆጣጠረና አዳዲስ ሠራዊቶችን እያስመረቀ ይገኛል።

Post image

በሌላኛው ጫፍ ደግሞ፤ የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መሪና አሁን የዲሞክራሲ ስምረት ትግራይ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ቆመዋል። ሁለቱም ወገኖች 'የፕሪቶሪያውን ሰላም ስምምነት አደጋ ላይ ጥለዋል' በማለት እርስ በርስ በመወነጃጀል ላይ ናቸው።

"ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ" የተሰኘው በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀስ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ከ"ትግራይ ናጽነት ጥምረት" ጋር በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ ስምምነቱ የትግራይን ጦርነት በማስቀረቱ የሰብዓዊ መብት ትልቅ ሚና እንደነበረው ገልጸዋል።

Post image

ነገር ግን፤ ሁለት ቁልፍ ጉዳዮች እንዳስፈጸሙ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዓለም በርኸ አንስተዋል። የመጀመሪያው በኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን መረጃ መሠረት በትግራይ ክልል ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው አለመመለስ ነው። ይህ ደግሞ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በተጨማሪ በሕገ መንግሥቱ እና በካምፓላ ስምምነት ጭምር የተረጋገጠ መብት ነው።

ተፈናቃዮችን የመመለስ ግዴታ በአዋጅ ጭምር የተቀመጠ ነው። ዋናው ኃላፊነትም በኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ በሰላም ሚኒስቴር እና በክልል መንግሥታት ላይ የሚያርፍ በመሆኑ፤ አቶ ተስፋዓለም ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

Post image

2ኛውና ዋነኛው ማጠንጠኛ የሽግግር ፍትሕ ወደ ሥራ አለመግባቱ ነው። የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር እንደተናገሩት፤ ይህ ሽግግር ፍትሕ እውነተኛ ፍትሕ ያመጣል የሚል እምነት ቀድሞውንም አልነበረም።

ስለዚህ፤ ከአነስተኛ አመራር እስከ ከፍተኛ የጦርነት ወንጀል ፈጻሚዎች በውጭ ወይም በሀገር ውስጥ ፍርድ ቤቶች ተገቢው ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት አስታውቀዋል።

ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ የፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸም "ግራ እንዳጋባቸው" ገልጸዋል።

Post image

ለዚህም ምክንያታቸው፤ በትግራይ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት አካላት ሳይሆኑ የማይመለከታቸው አካላት ደጋግመው ስለ ስምምነቱ ማንሳታቸው ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ተፈናቃዮች ጉዳይ ሲናገሩ ደግሞ፤ የዜጎች መመለስ ላይ ስምምነት ቢደረስም "ቁጥሩ እንደሚባለው አንድ ሚሊዮን ሳይሆን ከ300 ሺሕ እስከ 400 ሺሕ አይበልጥም" የሚል ሀሳብ አቅርበው ነበር።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን አስተያየት በተመለከተ አቶ ተስፋዓለም በርህ በሰጡት ምላሽ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ፖለቲካዊ አንድምታ እንዳለው ገልጸው፣ ስምምነቱ ባለቤት ያስፈልገዋል ብለዋል።

በተመሳሳይ የመንግሥት አካል የሆነው የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን '1 ሚሊዮን ተፈናቃይ አለ' ባለበት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት ቁጥር ተገቢ አለመሆኑንም አንስተዋል።

የድርጅቱ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መብሪህ ብርሃኔ በበኩላቸው፤ ተፈናቃዮች ለ5 ዓመታት በመጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ ስምምነቱን የፈረሙ አካላት ሙሉ ለሙሉ መተግበር አለባቸው ብለዋል።

Post image

በተለይም ተፈናቃዮች ሲመለሱ ደህንነታቸው መጠበቅ እንዳለበት አጽንዖት ሰጥተዋል። ለምሳሌም ወደ ወልቃይት አካባቢ ተፈናቃዮች ይመለሱ ሲባል፤ አሁን ያለው አስተዳደር ተጠያቂ መሆን ያለበት መሆኑንም አብራርተዋል።

አቶ መብሪህ አክለውም፤ የሽግግር ፍትሕ ተፈጻሚ መሆን ባለመቻሉ፣ ተጠያቂነት መስፈን አለበት ሲሉ ገልጸዋል።

ሕዝቡ ለእርቅ ዝግጁ ቢሆንም፤ ቅድሚያ ግን ተጠያቂነት መስፈን እንዳለበት አጽንዖት ሰጥተዋል።

ድርጅቱ ይህንን ተጠያቂነት ለማስፈን ጉዳዩን ወደ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደሚወስደው ገልጿል።

በትግራይ ብቻ ሳይሆን በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በሌሎች ክልሎች ያሉ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ እስካልተቻለ ድረስ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወሰድ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ተስፋዓለም ገልጸዋል።

የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በአየር መንገድ፣ በኤሌክትሪክ፣ በስልክና በባንክ የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶች ዳግም ተጀምረዋል።

እነዚህ መሠረታዊ ነገሮች ቢመለሱም፤ በዋናነት የተፈናቃዮች መመለስ እና የትግራይ ግዛታዊ አንድነት ጉዳዮች አሁንም ድረስ መልስ ያላገኙ አከራካሪ ጉዳዮች ሆነው ቀጥለዋል።

በትግራይ ዳግም ጦርነት እንዳይነሳም በህወሓትም ሆነ በፌዴራል መንግሥት በኩል ያሉ አካላት ከዚህ ድርጊት እንዲቆጠቡና አሁን ያለው ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ድርጅቱ ጥሪ አቅርቧል።

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሦስተኛ ዓመት መግባቱ በአንድ በኩል ጦርነቱ መቆሙን የምናይበት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ያልተፈቱ ወሳኝ ጉዳዮች አዲስ ቀውስ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ማስጠንቀቂያ የተሰጠበት ወቅት ነው።

በተለይም የአመራሩ መከፋፈል፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች አለመመለስ እና የሽግግር ፍትሕ አለመጀመር ዋና ፈተናዎች ሆነዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እነዚህን ጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ያደረጉት ጥረት የሰላሙን ዘላቂነት ለመጠበቅ ወሳኝ ነው።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ