ጥቅምት 13/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ያለበትን ከፍተኛ የውጭ ብድር ጫና ለማቃለልና የክፍያ ጊዜውን ለማራዘም ከአበዳሪ አካላት ጋር እየተደራደረ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ አስታውቋል።

ኮርፖሬሽኑ ያለበት የውጭ እዳ ጫና ከፍ ያለ ከመሆኑም ባሻገር፤ ከውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ሰፊ ችግር መፍጠሩ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የግብርናና የአግሮ-ፕሮሰሲንግ የፖርትፎሊዮ ዳይሬክተር ወይዘሮ አስማ ረዲ እንደገለጹት፤ ኮርፖሬሽኑ ካለበት የእዳ ጫና ተላቆ የሚፈለገውን ያህል የሎጅስቲክስ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።

ከእነዚህ ጥረቶች መካከል የውጭ እዳውን ለመክፈል የሚችለውን ጊዜ ለማራዘም መሞከር አንዱ ነው።

ዳይሬክተሯ አያይዘውም፤ የውጭ ብድር ወይም እዳውን በተቻለ አቅም መክፈል የሚችልበትን ጊዜ ለማራዘም በኮርፖሬሽኑ፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ከአበዳሪ አካላት ጋር ድርድር እየተካሔደ መሆኑን ለአሐዱ አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪ፤ የሀገር ውስጥ ብድሮችን ደግሞ ለማስተላለፍ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ወይዘሮ አስማ ጠቁመዋል።

አክለውም፤ ኮርፖሬሽኑ ውጤታማነታቸው በተረጋገጡ ኢንቨስትመንቶች ላይ ብቻ እንዲሳተፍ በማድረግ ራሱን ከአላስፈላጊ እዳ እንዲጠብቅ ለማድረግ በስፋት እየተሠራበት ይገኛል ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ ካለበት ብድር ባሻገር የጀመራቸው በርካታ ፕሮጀክቶች ፋይናንስ የሚጠይቁ መሆናቸውን ያነሱት ዳይሬክተሯ፤ እነዚህ በሙሉ ስኬታማ ሆነው ሲጠናቀቁ ኮርፖሬሽኑ በፋይናንስ ራሱን ችሎ የሚቆምበትን ዕድል በማስፋት የተሻለ አገልግሎትን እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከተቀላቀሉ ስምንት የልማት ድርጅቶች አንዱ መሆኑን ወይዘሮ አስማ ረዲ አስታውሰዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ