ጥቅምት 13/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት የ2018 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ይዘቶች ይፋ አድርጓል፡፡

ተማሪዎች፣ የተማሪ ቤተሰቦች፣ መምህራንና የትምህርት አመራር ለፈተና ዝግጅት በሚያደርጉበት ወቅት ፈተና የሚሸፍናቸውን የይዘት አካባቢዎች ማወቅ አስፈላጊ መሆኑ የገለጸው አገልግሎቱ፤ በመሆኑም የ2018 ትምህርት ዘመን 12ኛ ከፍል ፈተና ዝግጅትና አስተዳደርን አስመልክቶ መረጃ አውጥቷል፡፡

በዚህም መሠረት፡-
1. የትምህርት ዓይነቶችን በተመለከተ ለተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች እንግሊዘኛ፣ ሒሳብ፣ እስኮላስቲክ አፕቲትዩድ፣ ኬሚስትሪ፣ ፊዝክስና ባዮሎጂ፤

እንዲሁም ለማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች እንግሊዘኛ፣ ሒሳብ፣ እስኮላስቲክ አፕቲትዩድ፣ ታሪክ፣ ጂኦግራፊና ኢኮኖሚክስ መሆናቸው ተገልጿል።

2. ፈተናው ከ9ኛ እስከ 12ኛ ከፍል ደረጃዎችን እና በተማሪው መጽሐፍ ላይ ያሉትን ሁሉንም ምዕራፎች እንደሚሸፍንም ተመላክቷል፡፡

3. ከ10ኛ – 12ኛ ክፍል ሁሉም የትምህርት ዓይነት ፈተና በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት መሠረት እየተዘጋጀ ያለ ሲሆን፤ የ9ኛ ክፍል ደግሞ የሁሉም የትምህርት ዓይነቶች ፈተናዎች ከቀድሞውና ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርቶች የጋራ ይዘቶችን ብቻ አካቶ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡

4. ፈተናው ማንኛውም ተፈታኝ ተማሪ ከተማረው ሥርዓተ ትምህርትና ከተማሪው መጽሐፍ ላይ ብቻ ተመስርቶ እየተዘጋጀ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

5. የፈተናው አስተዳደር በበይነ መረብና በወረቀት ጎን ለጎን የሚሰጥ ሲሆን፤ አብዛኛው ተፈታኝ በበይነ መረብ እንዲፈተን እየተሠራ ያለ በመሆኑ ተፈታኞች እራሳቸውን በበይነ መረብ ለመፈተን ሊያዘጋጁ እንደሚገባ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አሳስቧል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ