ሰኔ 24/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ዝቅተኛ መስፈርቶችን ያላሟሉ ተቋማት ላይ እስከ መዘጋት የሚደርስ ቅጣት የሚያስከትለው የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የተካሄደው ግምገማ ውጤት፤ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ይፋ እንደሚደረግ የኢፌዴሪ ትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን አስታውቋል።

ባለሥልጣኑ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ 73 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የተካሄደው ግምገማ ማጠናቀቁን ገልጿል።

በባለሥልጣኑ የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ዳይሬክተር ቢንያም ኤሮ፤ "የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የጥራት ጉድለትን ለማሻሻል የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ እየተካሄደ ላለው ዳግም ምዘና ተቋማቱ እንዲያሟሉ የሚጠበቅባቸው ዝቅተኛውን መስፈርት በመሆኑ መመዘኛውን ለማሟላት አይከብዳቸውም" ብለዋል።

ዋና ዋናዎቹ የምዘና መስፈርቶችም ተቋማቱ የመማር ማስተማር ሂደቱን ባለሥልጣኑ ባስቀመጠው ደረጃ እና መስፈርት መሠረት ማከናወናቸው፣ ለማስተማር አላማ የሚውለው አካባቢ ለተማሪዎች በቂ ነጻ ቦታ ያለው እንዲሁም ምቹ እና ለተማሪዎች ቁጥር የተመጣጠነ መሆኑ እንደሆነም ገልጸዋል።

በተጨማሪም፤ ተቋማቱ ሙሉ የንግድ ፈቃድ ያላቸው፣ ለሚያስተምሩት እያንዳንዱ የትምህርት ዓይነት እውቅና የተሰጣቸው መሆኑ፣ ትምህርት ቤቱ የሚገኝበት ስፍራ ከጫጫታ የራቀና ለትምህርት አሰጣጥ የሚመች መሆኑ የምዘና መስፈርት ውስጥ መካተቱን አስረድተዋል።

እንዲሁም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋሙ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ምቹ መሆኑ እና በማስተማር ላይ የሚገኘው የተማሪ ብዛት እንዲያስተምር ከተፈቀደለት ጋር ያለው ልዩነት በግምገማው ወቅት ታሳቢ ከሚደረጉ ነጥቦች መካከል መሆናቸውን የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የግል ከፍተኛ ትምህርት እንዲሁም የቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና ተቋማት ማኅበር፣ ባለሥልጣኑ ባወጣቸው መመዘኛ መስፈርቶች ከትምህርት ጥራት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሌላቸው እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉንም ለማሟላት እንደሚቸገሩ በመግለጽ ቅሬታ ማሰማታቸውን አሐዱ መዘገቡ ይታወሳል።

ባለሥልጣኑ ለቅሬታው በሰጠው ምላሽ፤ "የተዘረዘሩት መስፈርቶች ከትምህርት ጥራት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ናቸው" ብሏል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ