ሰኔ 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች መካከል 46 በመቶ የሚሆኑት፤ በሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች አማካኝነት እንደሚደርሱ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ለአሐዱ አስታውቋል።
በክልሉ በሞተር ሳይክል አማካኝነት የሚፈጸም የትራፊክ አደጋ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የገለጹት በኮሚሽኑ የትራፊክ ፍስት ቁጥጥር ዳይሬክተር ኮማንደር ለማ ላቾሬ፤ መንጃ ፈቃድ ሳይኖራቸው የሚያሽከረክሩ ባለሞተሮች መብዛት እና ተሳፋሪን ከልክ በላይ ጭኖ ማሽከርከር ለአደጋው መንስኤ መሆኑን ተናግረዋል።
አያይዘውም፤ "ለአሽከርካሪዎች ጥበቃ ባለመኖሩ፤ ከሌሎች የተሽከርካሪዎች ግጭት ጋር ሲነፃፀር ልዩ ፈተናዎችን እና ከፍተኛ አደጋዎችን እያስከተለ ይገኛል" ብለዋል።
የባለ ሁለት እግር ሞተር ሳይክል ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ ሲገቡ እንዲመዘገቡና ደህንነታቸው እንዲረጋገጥ ማድረግ የሚያስችል አሰራር ቢዘረጋም፤ ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን የጠቆሙ ሲሆን፤ ለዚህም ችግር መባባስ አሽከርካሪዎች ለትራፊክ ፖሊስ ቁጥጥር አመቺ ባልሆነ ቦታ ማሽከርከራቸው አንዱ መሆኑን አብራርተዋል።
መንጃ ፈቃድ ሳይኖራቸው ሲያሽከረክሩ የሚገኙትን በቁጥጥር ሥር በማዋል፤ ሞተሩን ሕጋዊ መንጃ ፈቃድ ሲይዙ ብቻ ማስረከብ የሚቻልበት አሰራር እየተፈጠረ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
በክልሉ አደጋዎቹ በብዛት ከከተማ ወጣ ብለው ባሉ አካባቢዎች እንደሚከሰቱ የገለጹት ኮማንደር ለማ፤ "ሕብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ለመከላከል የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በተለያዩ አደረጃጀቶች እየተሰራ ነው" ብለዋል።
ወላጆች ለልጆቻቸው ሞተር ከመግዛታቸው በፊት የልጆቹን ዕድሜና መንጃ ፈቃድ የማሟላት ሂደትን የመጀመሪያ መስፈርት እንዲያደርጉ፤ በዕድርና በቤተ እምነቶች ጭምር የግንዛቤ ሥራ እየተሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በክልሉ 46 በመቶ የሚሆነው የትራፊክ አደጋ በባለ 2 እግር 'ሞተር ሳይክል' አሽከርካሪዎች አማካኝነት እንደሚደርስ ተገለጸ
