ሰኔ 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከጤና ባለሙያዎች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች ከጥያቄ ይልቅ አድናቆት እና ሙገሳ የበዛባቸው ነበሩ ሲሉ፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉ ተናግረዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረጉ ውይይቶች ውጤት እንዲመጡ ምን መደረግ አለበት? ከማን ምን ይጠበቃል? የሚል እና በተያያዥ ጉዳይዎች ላይ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ ከአሐዱ መድክ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

በቆይታቸውም "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በተከታታይ ያደረጓቸው ውይይቶች ከጥያቄ ይልቅ አድናቆት እና ሙገሳ የበዛባቸው ነበሩ" ብለዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተወከሉ ሰዎች በትክክል የሕዝብን ጥያቄ ስለማንሳታቸው እና የፖለቲካ ወገንተኛ አለመሆናቸው ሊፈተሸ እንደሚገባ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አንስተዋል፡፡

የሕዝቡ ጥያቄዎች የመልካም አስተዳደር፤ የኑሮ ውድነት፣የፍትህ እጦት፤የሰላም እና ሌሎች ጉዳይዎች መሆናቸውን ያነሱም ሲሆን፤ በውይይቱ ላይ የተጋበዙ ወይም የተወከሉ ሰዎች ውሀ የማያነሳ ለአንድ ሀገር መሪ የሚመጥን ጠንካራ ጥያቄ አለማንሳታቸውንም ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ ጥያቄ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ብቻ በሚደረግ ውይይት እንደማይመለስ ገልጸው፤ ችግሮች ያሉት ከታች ቀበሌ እና ወረዳ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፓርቲያቸው ውይይቱን ረግጦ መውጣቱን የገለጹት አቶ አበበ አካሉ፤ ጥያቄ ለማንሳት በሚፈለገው ልክ ዕድል አለመሰጠቱንም አንስተዋል፡፡

"በሚደረጉ ውይይቶች ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ካልተቻለ ማህበረሰቡ ያለው እምነት ከጊዜ ወደጊዜ እየተሸረሸረ ይመጣል" ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

የተነሱ ጥያቄዎች በየዓመቱ ተመሳሳይ መሆን እንደሌለባቸው ገልጸው፤ ምላሽ ለመስጠት ኃላፊነታቸውን የማይወጡ አመራሮች ካሉም ተጠያቂ ማድረግ እንደሚያስፍልግ ጠቁመዋል፡፡

አቶ አበበ አካሉ ከአሐዱ መድረክ ጋር ያደረጉትን ሙሉ ቆይታ ለመከታተል ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ!
👉 https://youtu.be/qhPxwwDvOqg?si=fqLVCL4qS2lVdVvq

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ