ሰኔ 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ እና ለሌሎች መሰል ሀገራት በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (USAID) በኩል ይከናወኑ የነበሩ ዕርዳታዎች እና ቁልፍ ተግባራት፤ አሁን በቀጥታ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር እንዲከናወኑ መደረጉ ተገልጿል።
እ.ኤ.አ. ከሰኔ 1 ቀን 2025 ጀምሮ፤ ተግባራዊ የተደረገው ይህ ሽግግር የተቀየሰው የእርዳታ ድግግሞሽን ለመቀነስ፣ ተጠያቂነትን ለማጠናከር እና የእርዳታ ፕሮግራሞችን ከአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ እና የብሄራዊ ደህንነት አላማዎች ጋር ለማጣጣም በማሰብ መሆኑ ተነግሯል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መረጃ መሠረት፤ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የተደረጉ የሁለትዮሽ ድጋፍ ስምምነቶች እንደተጠበቁ ይቀጥላሉ ተብሏል፡፡

በተለይም ሕይወት አድን የሆኑና ወሳኝ ድጋፎች ማለትም፤ የሰብዓዊ እርዳታ፣ የዓለም አቀፍ የጤና ድጋፍ፣ የምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ሳይስተጓጎሉ በአዲሱ መዋቅር ሥር ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተመላክቷል።
በፕሬዚዳንት ትራምፕና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጸሃፊ ማርኮ ሩቢዮ አመራር ዘመን የተጀመረው ይህ እቅድ፤ አሜሪካ የውጭ ዕርዳታዋን ብሄራዊ ጥቅሞችን በተሻለ መልኩ ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ የተቃኘ መሆኑም ተመላቷል።
ይህ ማስተካከያም በዓለም ዙሪያ የሕይወት አድን እርዳታን ለማድረስ የበለጠ ቀልጣፋ እና ስልታዊ አቀራረብን የሚከተል ስልታዊ እርምጃ መሆኑ ተነግሯል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ