ሕዳር 17/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እየታየ ያለውን የሰላም እጦት እና በጠብመንጃ የታገዘ ደም አፋሳሽ ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት፤ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ብልሐቶችን ተግባራዊ ማድረግ “ይበልጥ ውጤታማ ያደርገዋል” ሲል የኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማኅበር ገልጿል።
የማኅበሩ መስራች እና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጫላ አሰፋ፤ "ኢትዮጵያ ዓለም እየተጠቀመባቸው ከሚገኙት በውጤታማነታቸው የላቁና በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው የግጭት አፈታት ጥበባት አሏት" ሲሉ ለአሐዱ ሬዲዮ ተናግረዋል።
"ሀገሪቱን ቀድሞ ወደነበረችበት ሰላም መመለስ የሚቻለው እርቅ እና ሰላም የሚያመጡ ነባር እሴቶችን በመጠቀም ነው" ያሉት አቶ ጫላ፤ የውይይት መድረኮች ከውጭ ጥናቶች እና አስተሳሰቦች ይልቅ ለሀገር በቀል ዕውቀቶች ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማኅበር መስራች እና ስራ አስኪያጅ አቶ ጫላ በመጨረሻም፤ ወጣቱ ትውልድ በየአካባቢው ያለውን የግጭት አፈታት ሥርዓት በማጥናት ወቅታዊ ችግሮችን ፈትቶ ሰላማዊ አካባቢን ለመፍጠር እንዲተጋ ጥሪ አቅርበዋል።
ማኅበራቸውም ይህንን ታሳቢ በማድረግ ወጣቶች የሚወያዩበትና ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ሥነ ሥርዓቶችን የሚማሩበት መድረክ በመፍጠር እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን ሀገር በቀሉ የግጭት አፈታት ጥበብ የተሻለ ውጤታማ ይሆናል ተባለ