ሰኔ 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 የትምህርት ዘመን የ6ኛ ክፍል ከተፈተኑ 79 ሺሕ 34 ተማሪዎች መካከል 75 ሺሕ 85 ተማሪዎች ከ50 በመቶ በላይ ውጤት በማስመዝገብ ወደ ቀጣዩ ክፍል መሸጋገራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።

የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ የአጠቃላይ ካውንስል አባላት፤ የ2017 የትምህርት ዘመን የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የማለፊያ ውጤት 50 በመቶ እንዲሆን በዛሬው ዕለት ወስነዋል።

Post image

የትምህርት ቢሮው የቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዘላለም ሙላት በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በከተማ አስተዳደሩ ሥር ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት የማለፊያ ነጥብ በማምጣት ወደ ቀጣይ ክፍል ማለፋቸውን ገልጸዋል።

አያይዘዉ የአካል ጉዳተኞች ተማሪዎች የማለፊያ ነጥብ ከ45 በመቶ በላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ቢሮው ላለፉት ተከታታይ ሦስት ዓመታት የ6ኛ ክፍል ፈተና በመንግሥትና በግል ትምህርት ቤቶች በቀን እና በማታ የትምህርት መርሃግብር መስጠቱን ገልጸው፤ "የተያዘው ዓመት አፈጻጸም ከቀደሙት አንጻር ሲታይ ጥሩ የሚባል ነው" ብለዋል።

የትምህርት አሰጣጥ ስርአቱ ቴክኖሎጂን ጨማሮ ሬድዮ እና በቴሌቪዥንን በመጠቀም ሲሰጥ መቆየቱ ተማሪዎች ውጤታማነት እንዳገዘ ተገልጿል።

የትምህርት ቢሮው የቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዘላለም አክለውም፤ ዘንድሮው በከተማ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ተማሪዎች መካከል ከ1 እስከ 4 የሚሆኑት ከመንግሥት ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲናኦል ጫላ በበኩላቸው፤ በከተማ አስተዳደሩ 79 ሺሕ 34 ተማሪዎች ፈተናውን መውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡


#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ