ሰኔ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመንግሥትን የ2017 የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በዚህም "የጤና ባለሙያዎች ያነሱት ጥያቄ ምላሽ አላገኘም ፓለቲካ ተደርጎ ተወስዷል" በሚል ጥያቄ ከምክር ቤቱ አባላት ቀርቦላቸዋል።
በምላሻቸውም "የሀኪሞች ጥያቄ ውድቅ አልተደረገም። ፓለቲካ ብቻ አይደለም ነገር ግን የነሱ ጥያቄ ግን ለመሳፈር የሞከሩ ሰዎች ነበሩ ለይተን ነው ያስቀመጥነው" ሲሉ ገልጸዋል።
"ጥያቄያቸው ተገቢ ነው" ያሉ ሲሆን፤ በውይይቱ ወቅት ምላሽ ማግኘታቸውና መምህራንና የጤና ባለሙያዎች "የኢትዮጵያ ብልፅግና ለማረጋገጥ የእኛ ሥራ መስዕዋትነት ከፍሎ ልጆቻችንን ከድህነት ለመገላገል ስለሆነ አድራሽ ስለሆንን መከራውን እንቀበልና ኢትዮጵያን እናሻግር ተባብለን ተስማምተናል" ሲሉ ገልጸዋል።
ነገር ግን ጫናውን ለመቀነስ መንግሥት በተለያየ መልኩ ድጎማ ማድረጉን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዋጋ ግሽበትን ከፍላጎት ጋር ለማጣጣም የሚቻለው ገቢን ከፍላጎት ጋር ማጣጣም ሲቻል መሆኑን ጠቁመዋል።
"የሰውን ገቢ ለማሳደግ ደግሞ አጠቃላይ ዕድገቱን ማሳደግ የሚፈልግ ነው" ብለዋል።
አክለውም አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች መቸገራቸው ባይቀርም "እዳውን ተረክበናል፤ ስብራትን ተረክበናል እኛ ዋጋ ከፍለን ልጆቻችን ነፃ ይሁኑ ብለን ከወሰንን ያንን መከራ ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለብን" ሲሉ ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
"ከመምህራን እና የጤና ባለሙያዎች ጋር እኛ መስዕዋትነት ከፍለን ልጆቻችንን ከድህነት ለመገላገል ተስማምተናል" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
