ሰኔ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቋል! ክረምቱ ሲጠናቀቅ እናስመርቃለን። ግድቡ እንዳይመረቅ የሚያስችል ነገር አሁን የለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የመንግሥትን የ2017 የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ፤ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።

በዚህም "የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እንዳይመረቅ የሚያስችል ነገር አሁን የለም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ "ግድቡ ከመመረቁ በፊት ለመረበሽ የሚያስቡ ሰዎች አሉ እኛ ግን እናስመርቃለን" ሲሉ ተናግረዋል።

Post image

አክለውም "የግድቡ መመረቅ ለሱዳንም ሆነ ለግብፅ በረከት እንጂ ፍፁም ጉዳት አያመጣባቸውም" ሲሉ ገልጸው፤ "ለአብነትም በግብፅ አስዋን ግድብ አንድ ሊትር ውሃ አልቀነሰም" ብለዋል፡፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሚያመነጨውን ኃይል እና የአባይ ወንዝን በጋራ የመጠቀም ውጥን እንዳለም የገለጹ ሲሆን፤ ግድቡ ለማንኛውም አገራት ስጋት እንደማይሆን አስታውቀዋል።

"በግብጽም ሆነ በሌሎች አገራት ስጋት ሆኖ የሚነሳው ድርቅ ከሆነ፤ ድርቅን የመከላከሉን ስራ የአባይ ወንዝ መነሻ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ መስራት ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

"ኢትዮጵያ እስከበለጸገችና እስካደገች ድረስ የግብፅ እና የሱዳን ወንድሞቻችንን ጉዳት አንፈልግም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር ለመነጋገር፣ ለመደራደርና ለመስራት አሁንም ዝግጁ ነን" ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ስልጣን ያለው ምክር ቤት እንደመሆኑ ለግብፅ፣ ለሱዳን እንዲሁም ለተፋሰሱ ሀገራት መንግሥታት በሙሉ፤ መስከረም ወር ላይ ሕዳሴ ግድቡ ሲመረቅ የደስታችን ተካፋይ እንዲሆኑ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ