ጥቅምት 14/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ከ14 ዓመታት የግንባታ ሂደት በኋላ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በይፋ የተመረው ታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በኋላ በምዕራባዊ ግብጽ በሚገኘው የቶሽካ ሐይቅ የውኃ መጠን መጨመሩን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓይሻል ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
ኢንስቲትዩቱ ይህንን ይፋ ያደረገው 'ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የውኃ መጠን እንዲቀንስ አድርጓል' የሚሉ መረጃዎችን በተለያዩ መረጃ ማሰባሰቢያ ዘዴዎች ሐሰት መሆናቸውን እንዳረጋገጠ በመግለጽ ነው።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ ለአሐዱ እንደተናገሩት፣ በተፋሰሱ ሀገራት በኩል ከግድቡ ጋር ተያይዞ የውኃ መጠን መቀነስ አለ የሚሉ ቅሬታዎች ቢነሱም ሁኔታው ግን በተቃራኒው ነው።

ዳይሬክተሩ ውኃ በካናል ተጓጉዞ ተጨማሪ ሰው ሠራሽ ግድቦች መያዙንና ለዚህም በምዕራባዊ ግብፅ የቶሽካ ሐይቅ ላይ የታየው የውኃ መጠን መጨመር ዋነኛ ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።
አቶ አብዲሳ አክለውም፤ ከከርሰ ምድር፣ ከገጸ ምድር፣ ከግድቦች የውኃ የመያዝ መጠን፣ የሐይቆች ሽፋን እና ሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ የሳተላይትና የጂኦስፓይሻል መረጃዎችን አሰባስቦ ለልማት አስፈጻሚ ተቋማት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ የስፔስ ሳይንስ እና የጂኦስፓይሻል መረጃዎችን የማሰባሰብ ሥራዎችን የሚያከናውን ሲሆን፤ በዘጠኝ ማዕከላቱ በየዘርፉ መረጃዎችን እየለየ ለሚመለከታቸው አካላት ያቀርባል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ ካሉት 9 ማዕከላት አንዱ የውኃ መከታተያ ማዕከል፣ የከርሰ ምድር ውኃ እና የገፀ ምድር ውኃን ሁኔታ በሳተላይት መረጃዎች በመለየት ለሚመለከተው አካል ያቀርባል።
በተለይም የወንዞችን እና የሐይቆችን በጊዜ ሂደት ቦታ የመቀየር፣ የስፋት መጠን መቀነስ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይም መረጃ ይሰበስባል።
ከሕዳሴ ግድቡ ጋር ተያይዞም በንጋት ሐይቅ አቅራቢያ የተፈጠሩ ደሴቶችን ሁኔታ መረጃ መሰብሰብን ጨምሮ፤ የተፋሰሱ ሀገራት ቅሬታ የሚያሰሙባቸውን ጉዳዮች ሁሉ ኢንስቲትዩቱ መረጃ እንደሚያሰባስብ አቶ አብዲሳ ጨምረው ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ