ጥቅምት 19/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በጸጥታ ችግር ምክንያት ከቀደመ የመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ከ5ዓመታት በላይ በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን በአማራ እና ትግራይ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የክልል ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ገልጸዋል።
ማኅበራቱ በተለያዩ የክልሎቹ አካባቢዎች በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚኖሩ ተፈናቃዮችን ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ ለፌዴራልና ለክልል መንግሥታት በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርቡም፤ ዘላቂ መፍትሔ የሚያሰጥ ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰው ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መብሪህ ብርሃነ፤ "በክልሉ በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ 5 ዓመት እና ከዚያ በላይ የቆዩ ዜጎች አሉ" ብለዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ ለጥቂት ወራት ተብለው በተገነቡ መጠለያዎች ውስጥ ለዓመታት መቆየታቸውን አስታውሰው፤ ከፌደራልም ሆነ ከክልል መንግሥታት ዘላቂ መፍትሔ አለመሰጠቱ ነገሩን አሳሳቢ ደረጃ ላይ አድርሶታል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ሲቪል ማኅበራት ኅብረት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጋቱ ደስታ በበኩላቸው፤ በክልሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ገልጸው፤ ይህንን ያህል መጠን ያለው ተፈናቃይ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ድጋፍ ብቻ የሚፈታ ቀላል ጉዳይ አይደለም" ብለዋል።

አክለውም "የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀድሞ ቦታቸው ለመመለስ የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ ሰላም ነው። ተፈናቃዮቹ የሚመለሱበት አካባቢ ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑ መረጋገጥና ለጉዳዩ ኃላፊነት የሚወስድ አካል መኖር አለበት" ሲሉ አብራርተል።
በአጠቃላይ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ብቻ ከ2 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች ይገኛሉ ተብሏል።
የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ወደ መኖሪያቸው የመመለስ ጉዳይን ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩበት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ አሳስበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ