ጥቅምት 10/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ተቀጥራ ከምትሠራበት መኖሪያ ቤት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የወርቅ ጌጣጌጦችን የሰረቀችው የቤት ሠራተኛ በቁጥጥር ሥር ውላ ምርመራ እየተጣራባት መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል።
ተጠርጣሪ ብርቱካን ቢያድጌ የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመችው መስከረም 23 ቀን 2018 ዓ/ም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ወሎ ሰፈር አካባቢ ከሚገኝ መኖሪያ ቤት ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ነው።

ተጠርጣሪዋ በግል ተበዳይ መኖሪያ ቤት በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ ለዘጠኝ ወራት ያህል የሠራች ቢሆንም፤ በዕለቱ የአሠሪዋን መተኛት እንደምቹ ሁኔታ በመጠቀም በቁም ሳጥን ውስጥ ተቀምጦ የነበረ የአንገት፣ የእጅ፣ የጆሮ እና የጣት የወርቅ የብር እንዲሁም ወርቅ መሰል ጌጣጌጦችን፣ ሰባት የእጅ ሰዓቶችን፣ አምስት የተለያዩ ሞባይሎችን፣ አንድ ታፕሌት፣ አንድ ፓወር ባንክ፣ 12 ሺሕ 525 ብር እና 60 የእንግሊዝ ፓውንድ በአጠቃላይ 5 ሚሊዮን 258 ሺሕ 925 ብር የሚገመቱ ንብረቶችን በመስረቅ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 መካኒሳ አካባቢ ከሚገኝ አንድ ሆቴል አልጋ በመያዝ መደበቋን በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የባምቢስ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ገልጿል።

የግል ተበዳይ ንብረታቸው በቤት ሠራተኛቸው መሰረቁን ለፖሊስ ካመለከቱ በኋላ የባምቢስ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ከቆሬ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ጋር በመቀናጀት በተከናወነው የክትትል ሥራ ንብረቱን ይዛ ከተደበቀችበት ሆቴል ከእነ ኤግዚቢቱ በመያዝ ምርመራ እየተጣራባት መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።
በአንድ አንድ የቤት ሠራተኞች የሚፈጸሙ የስርቆት ወንጀሎችን አስቀድሞ ለመከላከል ህብረተሰቡ ሠራተኞችን ሲቀጥር ትክክለኛ አድራሻቸው የሚታወቅ እና ተገቢ ዋስትና በማቅረብ የሚችሉ መሆን አለባቸው ያለው ፖሊስ፤ ከተቀጠሩም በኃላ ተገቢውን ክትትል ማድረግ እንደሚገባም የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ መልዕክቱን አስተላልፏል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ