ሕዳር 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮ ቴሌኮም ከአዋሽ ባንክ ጋር በመተባበር በቴሌብር አማካኝነት የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትና አካታችነትን ያሳድጋል የተባለለትን "ጥላ" የተሰኘ የብድርና የቁጠባ አገልግሎት በትናትናው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል፡፡
በዚህ የአጋርነት ስምምነት መሰረትም አዋሽ ባንክ ለደንበኞች የ2 ቢሊዮን ብር የብድር አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታውቋል።
ሁለቱ ኩባንያዎች ለደንበኞች "ጥላ" የተሰኘ የብድርና ቁጠባ አገልግሎት፤ ባሉበት ሆነው የሚገኙበትን እድል የሚፈጥር ነው ተብሏል።

ይህ ጥላ ዲጂታል የብድርና ቁጠባ በተንቀሳቃሽ ስልክ የታገዘ የፋይናስ እና የዲቫይስ አገልግሎቶች ለመስጠት የተደረገው ስምምነት ሙሉ በሙሉ በሁለቱም ኩባንያዎች ተፈጻሚ የሚሆን ነው ተብሏል።
በዚህም መሰረት አዋሽ ባንክ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ለቴሌብር ደንበኞች የፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት የተስማማ የፋይናንስ ተቋም ሲሆን፤ ኢትዮ ቴሌኮም ደግሞ ከአዋሽ ባንክ ጋር በመተባበር ደንበኞች ከባንኩ የሚቀርበውን ብድር በድጂታል መንገድ ተደራሽ ያደርጋል ተብሏል፡፡

በዚህ የአጋርነት ስምምነት መሰረትም ደንበኞች የ15፣ የ40 እና የ75 ቀናት የብድር አገልግሎት መግኘት የሚችሉ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የብድርና የቁጠባ አገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚሆኑት የመንግሥትና የግል ተቋማት ላይ የሚሰሩ ሠራተኞች ሲሆኑ፤ ነገር ግን አገልግሎቱን ለማግኘት ሠራተኞቹ ደመወዛቸው በአዋሽ ባንክ እና በቴሌ ብር የሚከፈላቸው ከሆነ ብቻ ነው ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም የብድሩ ተጠቃሚ የሆኑ ደንበኞች ብድሩን በተሰጣቸው ቀነ ገደብ የማይከፍሉ ከሆነ፤ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ተከራክሮ የማስከፈል መብቱ የተጠበቀ እንደሆነ ተጠቁሟል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ