ሕዳር 4/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) እናት ባንክ አካታችነትን እና ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ሥርዓት በመዘርጋትና አይ-ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩትን አማካሪው በማድረግ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የፆታ ቦንድ ሽያጭ መዋቅር መጀመሩን አስታውቋል።
የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን በቦንድ ሽያጭ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ባንኩ የዛሬ 12 ዓመት የሴትችን ኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ ዓልሞ የተነሳ መሆኑን ተናግረዋል።

የቦርድ ሰብሳቢዋ "ይህም ጅምር እናት ባንክ ፋይናንስ የማግኘት ዕድል ላይ ያለውን የፆታ ክፍተት በቀጣይነት ለመድፈን ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል" ብለዋል።
በተለይም የፋይናንስ አቅርቦትን ለሴት ባለሙያዎች፣ ባለሀብቶች እና የማኅበረሰብ ክፍሎች በማዳረስ እኩልነት እና ዕድገትን ለማምጣት አዲስ መንገድ ይከፍታል ሲሉም ተናግረዋል።
የባንኩ ከ60 በመቶ በላይ የባለቤትነት ድርሻ፣ ከግማሽ በላይ የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ መቀመጫዎችን እና ከፍተኛ የአመራር ቦታዎች በሴቶች መያዙንም ወ/ሮ አስቴር ገልጸዋል።
ይህ የፆታ ቦንድ ሽያጭ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተደራሽነት የፆታ ክፍተትን ከ19 በመቶ ወደ 10 በመቶ ለመቀነስ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
አይ-ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ተወካይ ገመቹ ኦላና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ የእናት ባንክ በዚህ ዘርፍ አማካሪ በመሆን እንደሚያገለግል ገልጸው፤ በአፍሪካ ደረጃ ይህንን ዓይነት ቦንድ ጥቂት ሀገራት ብቻ ተግባራዊ ያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም የግብይት አማካሪ በመሆን የሚያገለግለው አይ ካፒታል፤ በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ የተመዘገበ የመጀመሪያው ድርጅት መሆኑን ተናግረዋል።
በእናት ባንክ የተጀመረው የፆታ ቦንድ ሽያጭ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው መሆኑን የገለጹት ተወካዩ፤ ይህ የብድር ሰነድ ለተወሰነ ዓመት የሚያገለግል መሆኑን ጨምረው ጠቁመዋል።
ድርጅታቸው ከእናት ባንክ ጋር ይህንን የተለየ ፆታን መሠረት ያደረገ የቦንድ ሽያጭ ለማስጀመር በግብዓት አማካሪነት በመስራቱ ደስተኛ መሆኑንም በመድረኩ ተናግረዋል።

ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ለተነሱ ጥያቄዎት ምላሽ የሰጡት የእናት ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኤርሚያስ አንዳርጌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ "አጠቃላይ ሂደቱ በዚህ ዓመት ሥራውን ይጀምራል" ብለዋል።
ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኃላም ፍቃድ ሲያገኝ ወደ ሥራ ይገባል ያሉት ሥራ ዋና አስፈፃሚው፤ ይህ ሂደት በአፍሪካ በኮትዲቯር እና በደቡብ አፍሪካ ተሞክሮ መኖሩን ተናግረዋል።
የጾታ ቦንድ ሽያጩ ሴቶች ለሚመሯቸው እና በባለቤትነት ለያዟቸው አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም ለኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ለግብርና እና ንግድ ሥራዎች እና ፆታዊ ለሆኑ ኢንተርፕራይዞች የረጅም ጊዜ ፋይናንስ ፕሮጀክቶች ላይ የሚውል መሆኑ ተገልጿል።
ቦንዱ የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን መመሪያዎች፣ የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋዮች መስፈርቶችን፣ የብሔራዊ ባንክ መመዘኛዎች፣ የዓለም ዓቀፋ የካፒታል ገበያ ማህበር (IርMA) እና የማህበራዊ ቦንድ መርሆዎችን መሠረት አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል።
በተጨማሪም ይህ ጅማሮ በብሔራዊ ባንክ ዕውቅና ላይ የተመሠረተ ነው የተባለ ሲሆን፤ ባንኩ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2025 በተካሄደው የመጀመሪያው የፆታ ፋይናንስ ተደራሽነት መረጃ ጠቋሚ ላይ ለውጥ አምጪ ደረጃ ያገኘ ብቸኛው የንግድ ተቋም ሆኖ ተመዝግቧል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ