ሕዳር 4/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) እ.ኤ.አ በ2050 በአፍሪካ የሚገኙ ሕጻናት ቁጥር ከ900 ሚሊየን በላይ እንደሚሆን መገመቱን፤ የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) አስታውቋል።
ስለሆነም የሕጻናት ጥቃትን ለመከላከል በጋራ አስቸኳይ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል ሲሉ፤ በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ምክትል ተወካይ አቡበከር ካምፖ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ምክትል ተወካዩ ይህን ያሉት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ 2024 በኮሎምቢያ ቦጎታ በሚንስትሮች ደረጃ በዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በሕጻናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን መከላከልና ምላሽ መስጠት ላይ በተከናወኑ ተግባራት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በተካሄደበት ወቅት ነው።
በመድረኩ በአፍሪካ 2050 ከ900 ሚሊየን በላይ የሕጻናት ቁጥር እንደሚኖር የገለጹት ተወካዩ፤ ይህም የዓለም 40 በመቶ የሚሸፍን መሆኑን በመግለጽ በአንድ በኩል ዕድል ሲሆን በሌላ በኩል ፈታኝ እንደሚሆን ተናግረዋል።
"ሕጻናቱ ጥበቃን ይሻሉ" ያሉም ሲሆን፤ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሕጻናት በመኖሪያ ቤታቸው፣ በትምህርት ቤት፣ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች እና በማህበረሰቡ ጥቃት ደርሶባቸዋል ብለዋል።
ለአብነትም በአውሮፓውያኑ ከ2018 በፊት በደቡብ አፍሪካ ከአምስት ሕጻናት አንዱ ለጥቃት ተጋላጭ እንደነበር አንስተዋል።
አክለውም የዚህና መሰል ጥቃቶች ከአጠቃለይ የሀገር ውስጥ ምርት 5 በመቶውን የሚያሳጣ ነው ብለዋል።
ስለሆነም የሕጻናትን ጥቃት መከላከል የሞራል ግዴታ ብቻ ሳይሆን አፍሪካ በ2063 አጀንዳ አንዱ ክፍል ነው ሲሉ ገልጸዋል። እንዲሁም በሕጻናት ላይ ኢንቨስት በማድረግ፣ የረጅም ጊዜ እቅዶችን በመያዝ ሕጻናትን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ጥሩ ሥራዎችን መስራቷን አነስተው፤ መንግሥትና አጋር አካላት በጋራ የመስራት ውጤት ማሳያ ነች ሲሉ አድንቀዋል።
ኮንፍረንሱም ከንግግሮች ባሻገር ወደ ተግባር መውረድ የሚችሉ እቅዶች የሚያዙበት ሊሆን እንደሚገባ አንስተዋል።
በተጨማሪም የአፍሪካ የሕጻናት መብትና ደህንነት ቻርተር 35ተኛ ዓመት ሲከበር በሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቆም እና እያንዳንዱ ልጅ ከጥቃት ነፃ ሆኖ የሚያድግበትን ከባቢ ለመፍጠር መሰራት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በ2050 በአፍሪካ የሚገኙ ሕጻናት ቁጥር ከ900 ሚሊየን በላይ እንደሚሆን ይገመታል ሲል ዩኒሴፍ ገለጸ
የሕጻናት ጥቃትን ለመከላከል አስቸኳይ እርምጃ መወሰድ አለበት ተብሏል