መስከረም 29/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) እስራኤል እና ሃማስ በግብፅ ለአራት ቀናት ሲያደርጉት ከቆዩት ድርድር በኋላ፤ የመጀመሪያ ዙር የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ መስምማታቸውን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትናንት ማምሻውን አስታውቀዋል፡፡
ትራምፕ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ስምምነቱ የእስራኤል ታጋቾች እና የፍልስጤም እስረኞች እንዲፈቱ፣ የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ እንዲወጡ እና እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም፤ "ይህ ለአረብ እና ለሙስሊሙ ዓለም፣ ለእስራኤል፣ በሀገራቱ ዙሪያ ላሉ መንግሥታት እንዲሁም ለአሜሪካ ታላቅ ቀን ነው" ያሉ ሲሆን፤ "ይህ ታሪካዊ እና ታይቶ የማይታወቅ ክስተት እንዲሆን አብረውን የሰሩትን የኳታር፣ ግብፅ እና የቱርክ አሸማጋዮችን እናመሰግናለን" ብለዋል፡፡
በኋላ ላይም ለፎክስ ኒውስ እንደተናገሩት፤ የስምምነቱ ምዕራፍ አንድ ከተተገበረ በኋላ፤ ጋዛ እንደገና ይገነባል፡፡ ከዚያ በኋላ "በጣም ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ ይሆናል" ሲሉ ገልጸዋል።
በተኩስ አቁም ስምምነቱ ዋነኛ አደራዳሪ የሆነችው የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ በእስራኤል የተያዙ አንዳንድ ፍልስጤማውያን እስረኞች እንዲፈቱ እና ሰብአዊ እርዳታ ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዲገባ ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቋል።
ይህንንም ተከትሎ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚኒ ኔታንያሁ በሰጡት መግለጫ፤ "ለእስራኤል ታላቅ ቀን ነው" ብለዋል።
"በእቅዱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ይሁንታ ሁሉም ታጋቾቻችን ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ይደረጋል" ያሉ ሲሆን፤ ይህ ለእስራኤል መንግሥት ዲፕሎማሲያዊ ስኬት፣ ሀገራዊ እና ሞራላዊ ድል ነው" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
"ከመጀመሪያው ግልጽ አድርጌያለሁ፡፡ ሁሉም ታጋቾቻችን እስኪመለሱ እና ሁሉም ግቦቻችን እስኪሳኩ ድረስ እረፍት አንኖረንም" ያሉት ኔታንያሁ፤ "በቆራጥ ውሳኔ፣ በጠንካራ ወታደራዊ እርምጃ እና በወዳጃችን እና አጋራችን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ታላቅ ጥረት በዚህ ወሳኝ የለውጥ ደረጃ ላይ ደርሰናል" ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ላደረጉት አመራር፣ አጋርነታቸው እና ለእስራኤል ደህንነት እና ለታጋቾቻችን ነፃነት ላሳዩት የማያወላውል ቁርጠኝነት እናመሰግናለን" ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ሃማስ በበኩሉ "ስምምነቱ በጋዛ ላይ የሚደረገውን ጦርነት የሚያበቃ፣ የወረራ ሃይሎች ሙሉ በሙሉ ለቀው እንዲወጡ፣ ሰብአዊ እርዳታ እንዲገባ የሚፈቅድ እና የእስረኞች ልውውጥን ተግባራዊ የሚያደርግ ነው" ብሏል።

"የጋዛ ሕዝብ ወደር የማይገኝለት ድፍረት፣ ክብር እና ጀግንነት አሳይቷል" ያለው ሃማስ፤ "ነፃነት እና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስካልተረጋገጠ ድረስ የሕዝባችንን ብሄራዊ መብት ፈጽሞ አሳልፈን አንሰጥም" ሲልም አስታውቋል፡፡
በዚህም መሠረት የእስራኤል መንግሥት በእቅዱ ላይ ድምጽ ለመስጠት በኢየሩሳሌም በዛሬው ዕለት ይሰበሰባል ተብሏል።
የመጀመሪያ ምዕራፍ ስምምነቱ በይፋ ተቀባይነት ካገኘ፤ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ወዲያውኑ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ ሙሉ ለሙሉ ለቀው እንደሚወጡ ተነግሯል፡፡
በማስከተልም "እስራኤል በመጀመሪያዎቹ አምስት ቀናት 400 የእርዳታ የጫኑ ተሸከርካሪዎች በየቀኑ ወደ ጋዛ እንዲገቡ ትፈቅዳለች" ሲሉ የፍልስጤም ከፍተኛ ባለስልጣን አስታውቀዋል፡፡
የዋይት ኀውስ ከፍተኛ ባለስልጣን ለሲቢኤስ ኒውስ እንደተናገሩት፤ እስራኤል ስምምነቱን ባፀደቀች በ24 ሰዓታት ውስጥ ጦሯን ከጋዛ ታስወጣለች። ጦር የማስወጣቱ ሂደት በተጠናቀቀ በ72 ሰዓታት ውስጥም ሃማስ በጋዛ ያሉትን ታጋቾች መልቀቅ ይጀምራል።
ሃማስ እስራኤል ላይ እ.ኤ.አ ኦክቶበር 7 ቀን 2023 ጥቃት በመሰንዘር 1 ሺሕ 200 እስራኤላውያንን መግደሉን ተከትሎ የተጀመረው የእስራኤል ሃማስ ጦርነት፤ ከትናንት በስተያ ድፍን ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡
ሃማስ አሁንም በጋዛ 48 ታጋቾችን መያዙ የተገለጸ ሲሆን፤ የእስራኤል መንግሥት ቢያንስ 20 ያህሉ በሕይወት እንዳሉ ሲያምን 28ቱ ሞተዋል ብሏል።
አብዛኞቹ በሃማስ ቁጥጥር ሥር የሚገኙት ታጋቾች የእስራኤል ዜጎች ሲሆኑ፤ አምስቱ የውጭ ሀገር ዜጎች (ሶስት ከታይላንድ አንድ ከታንዛኒያ አንድ ከኔፓል) ናቸው።
በጥቅሉ ኦክቶበር 7 ቀን 2023 251 ሰዎች ከእስራኤል የተወሰዱ ሲሆን፤ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ 148 ታጋቾች በህይወት ወደ እስራኤል ተመልሰዋል።
አብዛኛዎቹ በሃማስ የተለቀቁት በጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት ሲሆን፤ ስምንቱ ደግሞ የእስራኤል ጦር በከፈተው ዘመቻ የተመለሱ ናቸው ተብሏል።
እንዲሁም አምልጠው በእስራኤል ወታደሮች በስህተት የተገደሉትን ሦስት ታጋቾችን ጨምሮ፤ 59 አስከሬኖች ወደ እስራኤል መመለሳቸው ተነግሯል፡፡
በአሁኑ ወቅት በእስራኤል ወታደሮች ተይዘው ለእስር የተዳረጉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ 11 ሺሕ 100 ማለፉም እየተገለጸ ይገኛል
በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተደረገው የሰላም ማዕቀፍ የመጀመሪያው ምዕራፍ ስምምነት ቀሪዎቹን የእስራኤል ታጋቾች እና የፍልስጤም እስረኞች በፍጥነት ለመፍታት ያስችላል ተብሏል።

በሃማስና በእስራኤል ተወካዮች መካከል በግብፅ ለአራት ቀናት ከፍተኛ ድርድር ከተደረገ በኋላ የመጀመሪያ ዙር የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ውሳኔ ላይ መደረሱን ተከትሎም፤ በጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማውያን እና በእስራኤል የሚገኙ ታጋቾች የተገኘውን ድል በማክበር ላይ ይገኛሉ።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ