መስከረም 29/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዳዲስ ሕንጻዎች ግንባታ እና ነባር ሕንጻዎች እድሳትን ጨምሮ ከ500 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ከ24 ሺሕ በላይ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል።

የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር አበበ እሸቱ፤ በተለይም ባለፈው 10 ዓመት በከተማዋ ሰማይ ጠቀስ የሆኑ ትላልቅ ሕንጻዎች በስፋት እየተገነቡ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በ2017 በጀት ዓመትም ከቪላ ቤት እስከ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች አጠቃላይ ከ11 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ አዳዲስ ግንባታዎች ፈቃድ ተሰጥቶ ወደ ገበያው መቀላቀላቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከ2013 ጀምሮ እየተገነቡ የሚገኙ ከ12 ሺሕ በላይ ነባር ግንባታዎች ሲኖሩ፤ በድምሩ በከተማዋ ከ24 ሺህ በላይ ሕንጻዎች በመገንባት ላይ እንደሚገኙ ም/ዋና ዳይሬክተሩ ለአሐዱ አስታውቀዋል። የፕሮጀክቶቹ ወጪ ጥቅል ሲሰላ ከ500 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ እንደሆኑም ገልጸዋል።

የእነዚህም ሕንጻዎች ግንባታ፤ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ወይም ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት ከማንቀሳቀስ እና ከፍተኛ የሆነ የሥራ ዕድልን ከመፍጠር አንፃር የጎላ ጠቀሜታ እንዳላቸው ተናግረዋል።

Post image

በተጨማሪም የቤት አቅርቦትን በማስፋትና የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚያግዙ አንስተዋል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም በትልቅ በጀትና ወጪዎች የሚገነቡ በርካታ ሕንጻዎች ቢኖሩም፤ በሌላ መልኩ ደግሞ በሕንጻ ሥራ ላይ የሚደርስ አደጋም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መምጣቱን አንስተዋል።

በመሆኑም እነዚህ በመገንባት ላይ የሚገኙ ሕንጻዎችን በተመለከተ በሚፈለገው ልክ ደረጃቸውን ጠብቀው እየተሰሩ ስለመሆኑ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግባቸው አስታውቀዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ