ሰኔ 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ብሩህ ማይንድስ ኮንሰልት ከአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ እንዲሁም ከሌሎች የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ጋር በመተባበር፤ በአምስት ዓመታት ውስጥ ከ25 ሺሕ ለሚበልጡ ሥራ ፈጣሪዎች የስልጠና እና የማማከር አገልግሎት መስጠቱን አስታውቋል።
ተቋሙ ያዘጋጀውና ሰኔ 26 ቀን 2017 ጀምሮ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው "ልዩ ምልከታ የኢንተርፕርነርሺፕ ውይይት መርሃ ግብርና የገንዘብ አቅርቦት ለሥራ ፈጣሪ ኢንተርፕራይዞች" የተሰኘ አውደ ርዕይ በዛሬው ዕለት ተጠናቋል፡፡
ብሩህ ማይንድስ ኮንሰልት ከተመሰረተ አምስተኛ ዓመቱን ስለማስቆጠሩ የገለጹት የተቋሙ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰሎሞን ደሳለኝ፤ በእነዚህ ዓመታት በቀጥታ ለዜጎች የሥራ ዕድል የማመቻቸት ሥራ ባይሰራም ነገር ግን 25 ሺሕ ለሚደርሱ ሥራ ፈጣሪዎች ድጋፍ በማድረግ በሺዎች ለሚቆጠሩ ተቀጣሪዎች የሥራ ዕድል ማግኘት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።
ተቋማቸው የማማከር እና የስልጠና አገልግሎቱን የሰጠው አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ፤ በአዳማ፣ ሐዋሳና ወልዲያ ከተሞች ለሚገኙ ሥራ ፈጣሪዎች መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ አቶ ሰሎሞን በማብራሪያቸው፤ "በተጠቀሱት አካባቢዎች የነበሩና በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው የንግድ ተቋማት ወደነበሩበት የሥራ ዘርፍ እንዲመለሱ እና ከደረሰባቸው ኪሳራ እንዲያገግሙ የገንዘብ ድጋፍን ጨምሮ የስልጠና እና የማማከር ድጋፍ ተደርጎላቸዋል" ብለዋል።
የስልጠና ዘርፉ የቢዝነስ ፕሮፖዛል አዘገጃጀት፣ የአዋጭነት ጥናት፣ የሒሳብ መዝገብ አያያዝ እና መሰል ከቢዝነሱ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸውን ርዕሶች የሚያጠቃልል ሲሆን፤ ጥቃቅን እና አነስተኛ ቢዝነሶች ያለባቸውን የክህሎት ክፍተት መሙላት ላይ ያተኮረ ስለመሆኑ አቶ ሰሎሞን አብራርተዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ብሩህ ማይንድስ ኮንሰልት ከ25 ሺሕ ለሚበልጡ ሥራ ፈጣሪዎች የስልጠና እና የማማከር አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ
