መስከረም 29/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት በተያዘው ዓመት 11 አዳዲስ የስልጠና ፕሮግራሞችን መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በደረጃ 6 (የመጀመሪያ ዲግሪ)30 የሚደርሱ ፣ በደረጃ 7 (2ኛ ዲግሪ) ከ20 በላይ እና በደረጃ 8 (3ኛ ዲግሪ) ሁለት ፕሮግራሞች በመደበኛ፣ በቅዳሜ እና እሁድ እና በክረምት የስልጠና መርሀግብሮች ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጿል።
በዚህም ኢንስቲትዩቱ በተያዘው ዓመት የገበያውን ወይም ወቅቱ የሚፈልገውን የሙያ ዘርፍ መሠረት በማድረግ፤ በጥልቀት ተጠንተው የተለዩ በ11 የስልጠና ፕሮግራሞችን ለመስጠት ማቀዱን ገልጿል።

ከእነዚህም ፕሮግራሞች መካከል በሲቪል ቴክኖሎጂ፣ በአይሲቲ፣ በሳይበር ደህንነት፣ በግብርና፣ በአርቲፊሻል ኢንቲሊጀንስ፣ እንዲሁም፤ በመካኒካል ቴክኖሎጅ ዘርፎች የሰልጣኞችን አቅም ሊያሳድጉ የሚችሉ ስልጠናዎች በዘንድሮው ዓመት ከሚሰጡ ኮርሶች እንደሚጠቀሱ ኢንስቲትዩቱ ዛሬ ለብዙኃን መገናኛ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ፤ ኢንስቲትዩቱ ሰልጣኞችን በ4 መልኩ ተቀብሎ እንደሚያሰለጥን ገልጸዋል፡፡
በዚህም የቴክኒክና ሙያ አመራሮችን አሰልጣኞችን ደረጃዎችን ለማሻሻል እንደሚሰራ፣ የኢንዱስትሪ ቴክኒሺያኖችን በተለይም በማታው ቅዳሜና እሁድ ፕሮግራሞች እንደሚቀበል፣12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤትን ያመጡትን እንደሚቀበል እንዲሁም በተያዘው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የሬሜዲያል ተፈታኞችን እንደሚቀበል አስታውቀዋል።
ኢንስቲትዩቱ የሚሰጣቸውን የሙያና ቴክኒክ ስልጠናዎች፤ ሙያዊና ሥነ ምግባራዊ በተሞላበት መንገድ እንደሚሆንም ገልጸዋል።
ተደራሽነቱም አዲስ አበባ ከሚገኘው ዋናው ካምፓስ በተጨማሪ በሃዋሳ ካምፓስ፣ በብየዳ የስልጠና ልህቀት ማዕከል ካምፓሶች እንዲሁም በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ባሉ 16 የሳታላይት ተቋማት በደረጃ 6 ወይም በመጀመሪያ ድግሪ ስልጠና ለማህበረሰቡ እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም ኢንስቲትዩቱ በሀገሪቱ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ቁልፍ የስልጠና፣ የጥናትና ምርምር፣ የቴክኖሎጂ ማዕከል ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ የትምህርትና ስልጠና የብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 561/2017 በደረጃ 6 የመጀመሪያ ድግሪ፣ በደረጃ 7 የሁለተኛ ድግሪና በደረጃ 8 የሦስተኛ ዲግሪ መሆኑን ደንግጓል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ