ጥቅምት 14/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በቀጣይ ከተለያዩ የጎረቤት ሀገራት ጋር የሚደረገውን ትስስር የሚያጠናክር የባቡር መሠረተ ልማት ግንባታ ለመስራት በስፋት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታውቋል።

የትኞቹ ሀገራት ላይ ተግባራዊ የሚሆንና ምን ያክል ርቀት እንደሚኖራቸው ለማወቅ ገና በጥናት ላይ እንደሚገኙ የገለጹት፤ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሕሊና በላቸው (ኢ/ር) ናቸው።

Post image

በዚህ ዙሪያ ግን በቀጣይ ለመስራት የታሰቡ የተለያዩ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ያነሱት ዋና ሥራአስፈፃሚዋ፤ እንደየካሬ ሜትር እና ኪሎሜትር ርቀታቸው የተለያየ ዋጋን ሊጠይቁ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ትክክለኛ የሚፈጁት ዋጋም የመጨረሻ ዲዛይን ከተሰራና የሚደረጉ ጥናቶች ከተጠናቀቁ በኋላ የሚታወቅ እንደሆነ ተናግረዋል።

ነገር ግን በአማካኝ ከ3 እስከ 4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ሊፈጁ እንደሚችሉ ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ አስታውቀዋል።

እነዚህ ፕሮጀክቶችም ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚፈልጉ በመሆናቸው፤ ፋይናንስ በማፈላለግ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አመላከወተዋል።

በተጨማሪም የባቡር መስመር ግንባታ በራሱ ከፍተኛ ወጪን እንደሚጠይቅ የሚያነሱት ኢ/ር ሕሊና፤ ከተለያዩ አበዳሪ አካላት ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችል ሁኔታ እንደሚመቻች ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በባቡር መሠረተ ልማት ዙሪያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ትስስር በተመለከተ ከጅቡቲና ከኬንያ ጋር ያለውን የባቡር መስመር እንደማሳያ አንስተዋል።

ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት እየተሰራበት እንደሚገኝ ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ለአሐዱ አስታውቀዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ