መስከረም 19/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአሐዱ ሬድዮ ሥራ አስኪያጅ፣ የታሪክ ተመራማሪና ጋዜጠኛው ጥበቡ በለጠ ከሴጅ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የእውቅና ምስክር ወረቀትና ዋንጫ ተበርክቶለታል፡፡

ሴጅ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በተለያዩ አጫጭር የሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በትላንትናው ዕለት አስመርቋል።

ከተመሠረተ 3 ዓመታትን ያስቆጠረው ሴጅ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ዘርፍን ጨምሮ በ30 የትምህርት አይነቶች 380 ሰልጣኞችን ያስመረቀ ሲሆን፤ ከተመራቂዎች መካከልም ሕጻናት፣ ወጣቶች እና ጎልማሶች ይገኙበታል።

Post image

በዚሁ የምረቃ መርሐግብር ላይ የአሐዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆነውና በሙያው ለሀገር እና ለሕዝብ በርካታ አበርክቶት እያበረከተ ለሚገኘው ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፤ የክብር ካባ በማልበስ ከኢፌዴሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ) እጅ የእውቅና ምስክር ወረቀት እና ዋንጫ ተበርክቶለታል።

ሚኒስቴር ዲኤታው በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ይህ ሽልማት ጋዜጠኛ ጥበቡ በጋዜጠኝነቱ፣ በኪነ-ጥበቡ እና በታሪክ ምርምሩ ዘርፍ ለሀገሩ ላበረከተው አስተዋጽኦ የሚገባው መሆኑን ገልጸው፤ "ለወደፊቱም ጥሩ ማበረታቻ ይሆነዋል" ብለዋል።

Post image

የሴጅ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታዲዎስ ምስጋናው በበኩላቸው፤ ማሰልጠኛ ተቋሙ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በዘርፉ ለሀገር ካበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ በመነሳት "ይህንን የእውቅና ሽልማት ሲሰጥ ከፍተኛ ኩራት ይሰማዋል" ብለዋል።

ሽልማቱን በክብር የተቀበለው ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በበኩሉ፤ ለተበረከተለት ሽልማት ከፍተኛ ምስጋና በማቅረብ በቀጣይም በራሱ ፈቃድ የማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ የክብር አምባሳደር ሆኖ እንደሚያገለግል ቃል ገብቷል።

Post image

ሴጅ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በዘርፈ ብዙ የስልጠና ዘርፎቹ ላለፉት ዓመታት በማሰልጠን በሙያ ምዘና ብቃት አስመዝኖ በማብቃት ለገበያው ተወዳዳሪ የሆነ ባለሙያዎች በማበርከት ላይ የሚገኝ ተቋም መሆኑም በመድረኩ ተገልጿል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ