መስከረም 21/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ዓመታዊውን የአፍሪካ ኡደታዊ ስነምጣኔ ሆትስፖት (Africa Circular Economy Hotspot 2025) እንድታዘጋጅ መመረጧን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኡደታዊ ሥነ-ምጣኔ ሆትስፖት (ሰርኩላር ኢኮኖሚ ሆትስፖት) 2025 ማስጀመሪያ መድረክ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዝየም ተካሂዷል።

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ በዚህ ማስጀመሪያ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ይህን መድረክ እንድታዘጋጅ መመረጧ፤ ሀገሪቱ በአረንጓዴ ልማት ዙሪያ የምታደርገውን ተሳትፎ ለማንፀባረቅ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር አስታውቋል።

Post image

መድረኩ ትብብርን በማጎልበት ወደ ሰርኩላር ኢኮኖሚ ለሚደረገው ሽግግር በከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

ኡደታዊ ሥነ-ምጣኔ ዘላቂና አካታች ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ ሚና እንዳለው የገለጹት ዋና ዳይሬክሯ፤ ኡደታዊ ኢኮኖሚ ቆሻሻን መልሶ መጠቀም ካልተቻለ በአግባቡ መወገድ የሚችልበትን ሥርዓት መዘርጋት ስለመሆኑም አብራርተዋል።

አክለውም በዛሬው ዕለት የተካሄደው የማስጀመሪያ እና የምክክር መድረክ፤ በኢትዮጵያ እየተሰሩ ያሉ የከተሞች ልማት ውጤታማ የሃብት አጠቃቀም ዘላቂ አካባቢ አያያዝና አረንጓዴ ልማት ዙሪያ የምታደርገውን ተሳትፎ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

Post image

ዋና ዳይሬክሯ አክለውም፤ ኢትዮጵያ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ትኩረት አድርጋ እየሰራች የገለጹ ሲሆን፤ የኮሪደር ልማት፣ ጽዱ ኢትዮጵያና የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በጽዱ ኢትዮጵያ 30 ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን የተሳተፉበት ንቅናቄ መደረጉን ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ አካባቢን መጠበቅና ጽዳትን ማረጋገጥ ባህል ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ሰርኩላር ኢኮኖሚ ቆሻሻን መልሶ መጠቀምን በማበረታታት ከኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት ለማላቀቅ የሚያስችል ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡

የዚህ መድረክ አላማም ትብብርን በማጎልበት ወደ ሰርኩላር ኢኮኖሚ የሚደረገውን ሽግግር ለማፍጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።

ይህ መድረክ በሀገሪቱ መዘጋጀቱ የሀገሪቱን ገፅታ ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም አስታውቀዋል።

መድረኩን የአካባቢ ባለስልጣን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ያዘጋጀው መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ኡደታዊ ሥነ-ምጣኔ ሆትስፖት (ሰርኩላር ኢኮኖሚ ሆትስፖት) 2025 ማስጀመሪያ መድረክ ላይ ከሀገር ውስጥና ከአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ፖሊሲ አውጪዎች፤ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት፤ የኢንደስትሪ ተቋማት፤ የፈጠራ ባለሙያዎች እንዲሁም የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈውበታል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ