መስከረም 21/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በወንዶ ገነት ከተማ ትናንት መስከረም 20 ቀን 18 ዓ.ም "ሴት ልጅ ሱሪ አታደርግም'' በማለት ሴቶችን በማጥቃት፣ ልብሳቸውን በምላጭ በመቅደድና በማውለቅ ወንጀል የተጠረጠሩ ወደ 16 የሚጠጉ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የከተማው አስተዳደር አስታውቋል።
የከተማው አስተዳደር ባወጣው መግለጫ የከተማውን ለውጥ የማይፈልጉ ዕኩይ ተግባራቸውን ለመፈፀም በከተማው ውስጥ በቀን ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙትን የቀን ሠራተኞችን በመጠቀም ድርጊቱን መፈጸማቸውን አስታውቋል፡፡

እነዚህ ግለሰቦች "ሴት ሱሪ እንዳትለብስ በሽማግሌዎች ተወስኗል" በሚል ሽፋን ሴቶችን በነፃነት የመንቀሳቀስ መብታቸውን ለመጣስ ሙከራ አድርገዋል ያለው መግለጫው፤ "ሴት እህቶቻችን በፈለጉት ዓይነት አለባበስ ለብሰው በነፃነት የመንቀሳቀስ መብታቸዉን ለመጣስ የተሞከረዉ ሙከራ በመንግሥትና ሠላም ወዳድ በሆነው ህዝባችን ርብርብ በፍጥነት ሀሳባቸው ሳይሳካ ማክሸፍ ተችሏል" ብሏል።
ከተማ አስተዳደሩ በዚህ ዕኩይ ተግባር ላይ ተሳትፈዋል በሚል የጠረጠራቸዉን ግለሰቦች በሕግ ጥላ ስር አውሎ የምርመራ ሥራ እየሰራም እንደሚገኝ አስታውቋል።
የከተማው እንዲሁም መላው የክልሉ ነዋሪዎች የተከሰተውን ክስተት አጥብቀው የሚያወግዙ መሆኑን የገለጸው አስተዳደሩ፤ ከተማው ቀን ከሌሊት የንግድ እንቅስቃሴ ያለበት አከባቢ በመሆኑ ከክስተቱ በኃላ በደቂቃዎች ውስጥ እንደወትሮው በተረጋጋ መንፈስ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ የተመለሰ መሆኑን ገልጿል።
በቀጣይ ከተማ አስተዳደሩ የዚህ ጉዳይ መነሻ በማጣራት የእርምት እርምጃ እንደሚወስድ እንዲሁም ጥብቅ ክትትል እንደሚያደርግ አስታውቋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ