መስከረም 21/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ደረጃቸውን ያልጠበቁ በተለይ መፀዳጃ ቤት በሌላቸው እና ከታሸገ ውሃ ውጪ ያለ ክፍያ ከምግብ ጋር ንፁህ የመጠጥ ውሃ በማያቀርቡ ምግብ ቤቶች ላይ እርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ለአሐዱ አስታውቋል።
በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የምግብና ጤና ነክ ተቋማት ቁጥጥር ዳይሬክተር የሆኑት እስጢፋኖስ ጌታቸው ለአሐዱ እንደገለጹት፤ ማንኛውም ተቋምም ሆነ ግለሰብ ፍቃድ ተሰጥቶት ሥራ ከጀመረ በኋላ በምግብ ቤቶች ውስጥ ማሟላት ያለበትን ደረጃ እንዲያሟላ ይገደዳል።

አክለውም፤ ደረጃውን በማያሟሉ ምግብ ቤቶች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ወደ ተቋሙ የሚመጡ ቅሬታዎችና ጥቆማዎች መሠረት በማድረግ የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በምግብ ቤቶች የፅዳትና ንፅህና ጉድለት፣ መፀዳጃ ቤት አለመኖር እና የቧንቧ ውሀ አለማቅረብ ለተቋሙ ቅሬታ ከሚቀርቡ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸው፤ እነዚህን መሠረታዊ መስፈርቶች በማያሟሉ ምግብ ቤቶች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።

"እየተወሰደ ያለው እርምጃ እንደተቋሙ ይለያያል" ያሉት ዳይሬክተሩ፤ "ከቁርስ ቤቶች እስከ ባር ቤቶች ድረስ ከሚወሰዱ እርምጃዎች በተጨማሪ፣ ጤናማ ምርት በማያቀርቡ የምርት ማከፋፈያ ቤቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
መስሪያ ቤቱ በ11 ቅርንጫፍ እና 36 ክላስተር እየሰራ ሲሆን፤ ሕብረተሰቡ ደረጃቸውን ያላሟሉ ምግብ ቤቶች 8864 ላይ ነፃ የስልክ መስመር በመደወል ጥቆማ ማድረግ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ